ቀጥታ፡

የህዝብን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ርብርብ ይደረጋል -አስተዳደሩ

መተማና ሰቆጣ፤ መስከረም 4/2019 (ኢዜአ)፡- የህዝብን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን በላቀ ቅንጅትና ትብብር ለማስቀጠል ርብርብ እንደሚደረግ ተጠቆመ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን እና በዋግ ህምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የ2018 የበጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2019 ዓ.ም እቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እያሱ ይላቅ በገንዳ ውሃ ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ እንዳሉት፤ ባለፈው የበጀት ዓመት በተደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች አስተማማኝ ሰላም በመገንባት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት መስፈን የህዝቡ ንቁ ተሳትፎና ያልተቋረጠ ድጋፍ ቁልፍ ሚና መጫወቱን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ በግብርና ልማት፣ በገቢ አሰባሰብ፣ በከተማ ልማትና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተሻሉ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በተሻለ መልኩ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለው ማሩ በበኩላቸው፤ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ላሳየው አበረታች የልማትና የሰላም ፍላጎት ምስጋና አቅርበዋል። 


 

በ2019 የበጀት ዓመት የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦችን ለማሳካት የፓርቲው አመራርና አባላት ህዝቡን በንቅናቄ በማሳተፍ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

በተመሳሳይ በዋግ-ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በ2019 በጀት ዓመት የአካባቢን ፀጋ መሰረት ያደረጉ እቅዶችን አቅምን አሟጦ ለመስራት ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳግም ባይነሳኝ ናቸው።


 

በተጠናቀቀው ዓመት ውስብስብ ችግሮችን በመቋቋም በርካታ የልማት ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አስታውሰው፤ በአዲሱ  በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን በላቀ ደረጃ  ለመፈፀም የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

የአመራሩን ቅንጅታዊ አሰራር ይበልጥ በማሳደግ ህዝብን ያሳተፉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተግባራትን ማስፋፋት የአዲሱ በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ገልፀዋል። 

በየደረጃው የሚገኙ አስፈፃሚዎችም ተጨባጭና ውጤታማ እቅድ በማቀድና በመፈፀም ለስኬቱ ሊረባረቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሚካሄዱት መድረኮች የወረዳና ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም