ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና ዝግጅት

አዲስ አበባ፤መስከረም 4 /2019 (ኢዜአ):- ሁለተኛው የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና መስከረም 9 እና 10 ቀን 2019 ዓ.ም በዴንማርክ ኮፐንሃገን ይካሄዳል።

በሻምፒዮናው ላይ ከ86 ሀገራት የተወጣጡ 496 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

በተጨማሪም የዓለም አትሌቲክስ የስደተኞች አትሌቲክስ ቡድንም በዚህ ውድድር ላይ ተካፋይ ነው።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ ነች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።




የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ የቡድኑ መሪ ኢንስትራክተር አድማሱ ሳጂ እና የቴክኒክ ቡድኑ መሪ አቶ አሰፋ በቀለ በስታዲየሙ በመገኘት አትሌቶቹን አበረታተዋል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ለሻምፒዮናው የሚያስፈልገውን ዝግጅት ፌዴሬሽኑ ከወዲሁ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

አትሌቶቹ በትጋት እንዲዘጋጁ ያበረታቱ ሲሆን በኮፐንሀገን በሚያደርጉት ተሳትፎም መልካም ውጤት እንዲያስመዘግቡ ተመኝተዋል።

አትሌቶቹም ከኮፐንሀገን የአየር ንብረትና የውድድር ሁኔታ ጋር በተሻለ ሁኔታ ለመላመድ በእንጦጦ፣ በጣፎ፣ በ4 ሺህ አካባቢ፣ ቃሊቲ፣ ሰበታ እና ሰንዳፋን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች የልምምድ ዝግጅታቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ላይ በወንዶችና በሴቶች ግማሽ ማራቶን፣ በወንዶችና በሴቶች አምስት ኪሎ ሜትር እንዲሁም በሴቶች አንድ ማይል ውድድሮች ተሳትፎ ታደርጋለች።




የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የቀድሞውን የዓለም አትሌቲክስ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የተካ ውድድር ነው።

የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናው ከእ.አ.አ 1992 እስከ 2020 ሲካሄድ ቆይቷል።

እ.አ.አ በ2023 ስያሜውን ቀይሮ የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የተባለ ሲሆን የመጀመሪያው ውድድር በዛው ዓመት በላቲቪያ ሪጋ ተካሄዷል።

የአሁኑ ሻምፒዮና ከዚህ ቀደም ከነበረው የግማሽ ማራቶን በተጨማሪ የአምስት ኪሎ ሜትር እና የአንድ ማይል ውድድሮች ተካተውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም