ቀጥታ፡

ሊድስ ዩናይትድ ከኒውካስትል ዩናይትድ: የአራተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 4/2019 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።

ምሽት አራት ሰዓት ላይ ሊድስ ዩናይትድ ከኒውካስትል ዩናይትድ በኤላንድ ሮድ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባለሜዳው ሊድስ ዩናይትድ ከሶስት ጨዋታዎች አምስት ነጥብ በማግኘት 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ኒውካስትል ዩናይትድ በተመሳሳይ አምስት ነጥብ በግብ ክፍያ በልጦ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በሊጉ 30 ጊዜ ተገናኝተው ኒውካስትል ዩናይትድ በ13ቱ ድል ሲቀናው ሊድስ ዩናይትድ ሰባት ጊዜ አሸንፏል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።

ኒውካስትል ዩናይትድ በ30ዎቹ ጨዋታዎች ላይ 45 ግቦችን ሲያስቆጥር ሊድስ ዩናይትድ 42 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ቡድኖቹ ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው ኒውካስትል ዩናይትድ በሁለቱ ሲያሸንፍ በቀሪ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ሊድስ ዩናይትድ ኒውካስትልን ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ ያሸነፈው እ.አ.አ በ2021 ሲሆን በወቅቱ የ2 ለ 1 ድል ተቀዳጅቷል።

ባለሜዳው ሊድስ ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። ኒውካስትል ዩናይትድ በሶስተኛ ሳምንት ከቦርንማውዝ ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል።

ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የ41 ዓመቱን ማይክል ሳሊስበሪ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት እንዲመሩ ተመድበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም