በባህር ዳር ከተማ አስተማማኝ ሰላምና ተጨባጭ የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ አስተማማኝ ሰላምና ተጨባጭ የልማት ስራዎችን ማከናወን ተችሏል
ባህር ዳር፤ መስከረም 4/2019 (ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው አስታወቁ።
«አርቆ ማየት፤ አልቆ መሥራት» በሚል መሪ ሐሳብ የመንግሥትና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ መካሄድ ጀምሯል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በዚሁ መድረክ እንደገለጹት፤ በከተማዋ የፀጥታ አካላትና በሕዝቡ ጠንካራ ቅንጅት አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን ተችሏል።
ባህር ዳርን ውብ፣ ጽዱ እና አረንጓዴ የማድረግ ተግባር በተጨባጭ እውን ማድረግ መቻሉንና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ መቀየራቸውን ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶችም አዲስ የሥራ ባህል ተፈጥሮባቸው በአጭር ጊዜና በጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጉንም አንስተዋል።
በከተማዋ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት በመስጠት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን ከ75 ሺህ በላይ ነዋሪዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን በበኩላቸው፤ በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ አስተማማኝ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱን ገልጸዋል።
የተገኘው ሰላም ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች መሳካት ቁልፍ መሠረት በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁለንተናዊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የታዩ ክፍተቶችን በማረም በአዲሱ በጀት ዓመት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብና ከተማዋን ይበልጥ ለማልማት ሁሉም በቅንጅት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።