ሰላምን በማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ደሴ/ደብረ ብርሃን፤መስከረም 4/2018 (ኢዜአ)፡- በአካባቢው የተገኘውን ሰላም በማጽናት ህብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
የደቡብ ወሎ ዞን፣ የደሴና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደሮች የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ባለፈው በጀት ዓመት ሰላምን በማስጠበቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።
በተለይም በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በማዕድን ሀብት ልማት፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንት እና በሌሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም ህብረተሰቡን በማሳተፍና ሰላምን በማጽናት የተጀመረውን ብልጽግናን የማረጋገጥ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ ዳኜ በበኩላቸው፣ ባለፈው በጀት ዓመት በፓርቲና በመንግሥት ውጤታማ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን ተችሏል።
ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ከማካሄድ ባለፈ በሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ሥራዎችን ማከናወን መቻሉንም ለአብነት አንስተዋል።
በተመሳሳይ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ እንዳሉት፣ የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬታማ የልማት ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።
በተለይ በኮሪደር ልማት፣ በ"ስማርት ሲቲ" ግንባታ፣ በመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት፣ በቴክኖሎጂና በሌሎችም የተመዘገቡ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በተከናወኑ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች አበረታች ውጤት መመዝገቡን የገለጹት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።
በተያዘው በጀት ዓመትም የከተማዋን ሁለገብ ዕድገት ለማፋጠን የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችና ስኬቶችን በማስፋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የልማት ሥራዎች በልዩ ትኩረት ይከናወናሉ።
በዚህ በጀት ዓመት ከ23 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፣ ለውጤታማነቱም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጌታቸው እንዳሉት፤ በአዲሱ በጀት ዓመት የዕድገትና አሻጋሪ ዕቅድ ግቦች ስኬታማ እንዲሆኑ በትኩረት ይሠራል።
በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥና ልማት እንዲፋጠን የሕዝብ አንድነትን በማጠናከር የተረጋጋ ሰላም የማስፈን ሥራው ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ።
በየከተሞቹ በሚካሄደው መድረክ የፓርቲና የመንግሥት ዕቅዶች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን፣ በመድረኩም የዞን ፣ የከተማ፣ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።