ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦቱን በእጥፍ በማሳደግ የቀጣናውን የኢኮኖሚና የኃይል ትስስር እያጠናከረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦቱን በእጥፍ በማሳደግ የቀጣናውን የኢኮኖሚና የኃይል ትስስር እያጠናከረ ነው
አዲስ አበባ፤መስከረም4 /2019 (ኢዜአ):-ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከእጥፍ በላይ ከማሳደግ ባለፈ የቀጣናውን የኃይል ትስስር እያጠናከረ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አስታወቁ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ጽናት፣ አንድነትና ቁርጠኝነት በተግባር የተገለጠበት «ዳግማዊ ዓድዋ» መሆኑን ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የላቀ ስኬት ማስመዝገብ እንደምትችል ለዓለም ያስመሰከረችበት፤ ብሎም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ታላቅ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ ተመርቆ ወደ ሙሉ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የሀገሪቱን የኃይል ማመንጨት አቅም በእጥፍ ከመጨመሩም በላይ፣ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በእጅጉ ማሳደጉን ገልጸዋል።
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ ካገኘው ከፍተኛ ገቢ በተጨማሪ ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘቱን ጠቁመው፤ ለዚህ ታሪካዊ ስኬት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዕዳ ተላቆ ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገር ማስቻሉን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በተመጣጣኝ ዋጋ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እያቀረበች መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የግድቡ ወደ ሥራ መግባት ለቀጣናዊ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር ማደግ አይነተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለኬንያ፣ ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እና በከፊል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ መሆኗን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ወደ እነዚህ ሀገራት ከሚላከው አጠቃላይ ኃይል ውስጥ 52 በመቶ የሚሆነው ድርሻ ከህዳሴው ግድብ የሚመነጭ መሆኑን አመላክተዋል።
የኃይል አቅርቦቱን በእጥፍ በማሳደግ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራትም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ጥቅም እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።