በጅማ ዞን የተቀናጀ የቡና ልማትና የጥራት እንክብካቤ ስራን በስፋት በመተግበር አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን የተቀናጀ የቡና ልማትና የጥራት እንክብካቤ ስራን በስፋት በመተግበር አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ሆነዋል
ጅማ፤ መስከረም 4/2019 (ኢዜአ)፡- በጅማ ዞን የተቀናጀ የቡና ልማትና የጥራት እንክብካቤ ስራን በስፋት በመተግበር ከምርቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ።
በጅማ ዞን ቀደም ሲል የሚሰበሰበው የቡና ምርት በጥራትና በድህረ-ምርት አያያዝ ጉድለት ምክንያት አርሶ አደሩን በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳያደርግ ቆይቷል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ በዞኑ አመራርና ባለሙያዎች አስተባባሪነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተቀናጀ የቡና ልማትና የጥራት ማሻሻያ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷል።
በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑት አርሶ አደሮች እንዳሉት፣ ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት በቀጥታ ለገበያ የሚያቀርቡበት አሰራር በመዘርጋቱ፣ ከቀጥታ የገበያ ትስስሩ የሚገኘው ገቢ ተጠቃሚነታቸውንና የኑሮ ደረጃቸውን እንዲሻሻል አድርጎታል።
በዞኑ የጎማ ወረዳ አርሶ አደር ሙስጠፋ አባ ቀኖ፣ በአሁኑ ወቅት መንግስት ባመቻቸው የቀጥታ የገበያ እድል የደላሎች ጣልቃ ገብነት በመቅረቱ፣ ቡናቸውን በጥራትና በስፋት አዘጋጅተው ለገበያ ማቅረብ መቻላቸውን ተናግረዋል።
ቡናን በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፣በጥራት እና በቴክኖሎጂ በተደገፈው አሰራር ከአንድ ሄክታር እስከ 10 ኩንታል ምርት በማግኘት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አሰራሩ ገቢያቸውን ከማሳደጉም በላይ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግኝት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ማስቻሉንም አብራርተዋል።
ሌላኛው የዞኑ አርሶ አደር ዛኪር አባፊጣ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ከተለምዷዊ አሰራር በመላቀቅ ቡናን በኩታገጠም በጥራት ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
በኩታገጠም የሚከናወነው የልማት ስራ የሙያና የቴክኖሎጂ ድጋፍን በጥንቃቄ ለመተግበር በመርዳቱ፣ የምርት ጥራትንና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳደገው ገልጸዋል።
በቡና ልማት ትርፋማ መሆናቸውን የገለጹት አርሶ አደር ዛኪር፣ ከዘርፉ ባገኙት ገቢ በቅርቡ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ጠቅሰዋል።
ይህም በጥራትና በኩታገጠም የተመራ የግብርና ልማት አርሶ አደሩን ወደ ባለሃብትነት ለማሸጋገር ያለውን አቅም ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣት አርሶ አደር ቡሊ አባመጫ በበኩሉ፣ ቡናን በጥራት በማምረት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።
በቅርቡ በተጠናቀቀው የቡና ምርት ዘመን ከ20 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ጥራት ያለው ቡና ለገበያ ማቅረቡንና ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ የሚያጎለብት መሆኑን አብራርቷል።
አርሶ አደር ኤሊያስ አባሰዲም፣ ከዚህ በፊት ከሚያመርቷቸው የቡና ተክሎች በተጨማሪ በየወቅቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ምርጥ ዘር የቡና ችግኞች ፍሬ አፍርተው ምርት መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
አሰራሩ የቀደመውን የምርት አቅም በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ገልጸው፤ ይህም የምርት መጠናቸውንና አምራችነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ከፍ እንዳደረገላቸው ገልጸዋል።
አርሶ አደሮቹ እንደገለጹትም፣ መንግስት ለቡና ምርት ጥራትና መስፋፋት በሰጠው ትኩረት አማካኝነት አስፈላጊው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል መደረጉ ለቡና ልማቱ መስፋፋትና ለውጤታማነቱ ዋና ምክንያት ነው።
የጅማ ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቲጃኒ ተማም እንደገለጹት፣ በዞኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት የቡና ምርት ሽፋን ከ330 ሺህ ሄክታር ወደ 700 ሺህ ሄክታር አድጓል።
የቡና ልማት ሽፋኑ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ ምርታማነትንና የጥራት ደረጃን ከመጨመሩ ባሻገር የአርሶ አደሩን የገቢ አቅም ያጎለበተ መሆኑንም አብራርተዋል።
አርሶ አደሩ ምርቱን በቴክኖሎጂና በኩታገጠም በጥራት በማልማት ያለምንም ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ለገበያ የሚያቀርብበት ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል ብለዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው ዓመት ከተሰበሰበው 341 ሺህ ቶን ቡና ውስጥ 94 ሺህ ቶኑ ለዓለም አቀፍ ገበያ የቀረበ ሲሆን፣ ይህም ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባሻገር አርሶ አደሩን የኢንቨስትመንት ባለቤት እስከ መሆን ያደረሰ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።