የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የከፍታ ጉዞ ማሳያ - ብሪክስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የከፍታ ጉዞ ማሳያ - ብሪክስ
''የብሪክስ ጉባዔ የጋራ ትብብርን ወደ የጋራ እሴት፣ ጽናት እና ዘላቂ ዕድገት የመለወጥ ሰፊ አቅምና ቁርጠኝነት አለው" በማለት ነው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ18ኛው የብሪክስ ጉባዔ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር።
18ኛው የብሪክስ ጉባኤ የጥምረቱ አባል ሀገራት መሪዎች በተገኙበት “ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርንና ዘላቂነትን መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ በህንድ ኒውዴልሂ እየተካሄደ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የልዑክ ቡድናቸው በዚሁ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በሚፈጥረው ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የልዑክ ቡድናቸው የብሪክስ ጉባኤ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።
ብሪክስ ለአፍሪካ ቀጣና እና በተለይም ለኢትዮጵያ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅሞችን የሚያስገኝ አዲስ የዓለም ስርዓት እየተፈጠረበት የሚገኝ ጥምረት ነው።
የብሪክስ ጥምረት ለኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። በዚህም እንደ ቻይና፣ ህንድ እና ሩሲያ ካሉ ታላላቅ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በተለይም በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና በኢነርጂ ዘርፍ በማሳደግ በኩል አይነተኛ አማራጭ የኢንቨስትመንት መንገድ ነው።
ጥምረቱ ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ትሩፋት አንጻር ሲታይ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በመቅረፍ፤ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር በሚደረጉ የንግድ ልውውጦች የሀገር ውስጥ ገንዘብን የመጠቀም ዕድልን ስለሚፈጥር፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት እጥረትን ከመቀነስ አኳያም እንዲሁ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅዷ ኢኮኖሚዋን በመሠረታዊነት ለሚያሳድጉ መሠረተ ልማት ግንባታ እና ማስፋፊያ እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ሽግግር ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች። ከዚህ አኳያ ብሪክስ የመንገድ፣ የባቡር፣ የኃይል ማመንጫዎችና ዲጂታል ቴክኖሎጂ እና መሰል የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ በማመቻቸት በኩል ኢትዮጵያ ለያዘችው ግብ ስኬት ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ጥምረት ነው።
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ላሳካቻቸው ውጤቶች የዓለም አቀፍ ግንኙነቷን የቃኘችበት አዲስ አካሄድ ተጠቃሽ ነው።
ከእነዚህ ስኬቶች መካከል ደግሞ በብሪክስ ጥምረት ውስጥ አባል የሆነችበት መንገድ አንዱ ሲሆን፤ ይህ የብሪክስ ጥምረት ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት የራሱን ሚና በመጫወት ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአህጉሪቷ ያላትን መሪነትና ዲፕሎማሲያዊ የበላይነት በማጠናከር በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ድምፅ እንድታጎላ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እንዲያድግ እያስቻለ መሆኑም በተጨባጭ ታይቷል።
የብሪክስ ጥምረት በአፍሪካ አለፍ ሲልም በጥምረቱ አባል ሀገራት መካከል ተመጣጣኝ ልማት እንዲኖር እና ሀገራቱ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ አስቻይ ምህዳር እየፈጠረም ይገኛል። በተለይ አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በማልማት የኢኮኖሚ ዕድገቷን እንድታፋጥን አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ መሆን የሚያስችለውን አደረጃጀት እና አሰራር እየዘረጋም ይገኛል።
ይህ የጥምረቱ አዳዲስ አደረጃጀት እና አሰራር አዲሱ የልማት ባንክ እንዲወለድ አስችሏል። በዚህ ባንክ አማካኝነት የአፍሪካ ሀገራት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ጥብቅ መስፈርቶች ነፃ በሆነ መንገድ ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ ወይም ብድር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
በጥምረቱ አማካኝነት የተፈጠረው አዲሱ የልማት ባንክ የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው ሀገራዊ ገንዘብ እና ከአሜሪካ ዶላር ተጽእኖ ውጪ ከታላላቅ የብሪክስ ሀገራት ጋር የንግድ ልውውጥ እንዲያከናውኑ በር እየከፈተ ይገኛል። በተጨማሪም አፍሪካ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ የውሳኔ መድረኮች ላይ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት በማሳደግ፣ ፍትሐዊ የሆነ የዓለም አቀፍ ስርዓት እንዲፈጠር እያስቻለ መሆኑም የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ሰነባብቷል።
ይህ የብሪክስ ጥምረት መመስረት፣ መስፋፋትና መጠናከር በዓለም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስርዓት ላይ በርካታ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጦችንና አንድምታዎችን እያስከተለ ይገኛል።
የብሪክስ ጥምረት ተመስርቶ እየፈጠረ ያለው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ተጽዕኖ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የምዕራባውያን ሀገራት በዓለም ፖለቲካ ላይ የነበራቸውን የበላይነት በመገዳደር፣ ሥልጣንና ውሳኔ ሰጪነት ለተለያዩ የአህጉራት ኃይሎች እንዲከፋፈል፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ የአሰራር እና የአደረጃጀት ማሻሻያ ጥያቄዎች ጎልተው እንዲሰሙ የማድረግ አቅም እየፈጠረ ነው።
በተጨማሪም የብሪክስ ጥምረት አባል ሀገራት በንግድ ልውውጣቸው ወቅት በራሳቸው ሀገራዊ ገንዘቦች የመጠቀም ዝንባሌያቸው በመጨመሩ፣ የአሜሪካ ዶላር በዓለም ንግድና መጠባበቂያ ክምችት ላይ ያለውን ፍጹም የበላይነት በማዳከም፤ አዲሱ ልማት ባንክ የብሪክስ የድንገተኛ የገንዘብ ድጋፍ ማዕቀፍ የምዕራባውያኑን ጥብቅ የፖለቲካ መስፈርቶች ሳይከተሉ ለታዳጊ ሀገራት ፕሮጀክቶች ፋይናንስ እንዲያቀርቡ ብሎም የብሪክስ አባል ሀገራት የዓለምን ከፍተኛ የነዳጅ፣ የጋዝ፣ የብረታ ብረት እና የግብርና ምርቶች አቅርቦት የሚቆጣጠሩ በመሆናቸው፣ በዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች እና የዋጋ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን እያሳደገ መጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ ያላቸውን የመልማት አቅም ለመጠቀም አማራጭ የልማት ፋይናንስ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል። ለዚህ ደግሞ የብሪክስ ጥምረት ይዞት የመጣውን ዕድል በውል አንስተዋል።
ለዚህም ነው በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን፤ አሁን ያለው መልካም ዕድል እነዚህን አቅሞች በማስተሳሰር የላቀ እሴት መፍጠር እና ይህ እሴት ደግሞ ሀብቱ በሚገኝበት ቦታ መመረት እንዲችል ማድረግ ነው ሲሉ ያመላከቱት።
ኢትዮጵያ በማዕድን ልማት፣ በታዳሽ ኃይል እና እያደገ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መሠረቷ ላይ እነዚህን አጋርነቶች ለመገንባት ዝግጁ መሆኗን ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሠራር ሥርዓቶቻችን ውስጥ ጽናትን መገንባት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የአህጉራችንን ፍላጎት እንዲያገለግል ማድረግ፣ አስተማማኝ የዕዳ እፎይታ ሒደትን ማሳደግ እንዲሁም የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራዎችን ከኢኮኖሚ ሽግግር ጋር ማስተሳሰር ከጥምረቱ የሚጠበቅ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የብሪክስ ጉባዔ የጋራ ትብብርን ወደ የጋራ እሴት፣ ጽናት እና ዘላቂ ዕድገት የመለወጥ ሰፊ አቅምና ቁርጠኝነት አለው። የጥምረቱ አቅም ከተናጠል አካሄድ ይልቅ ትብብርና ለጋራ እሴት መጎልበት ያለውን ዕድል ያመላክታል።
ኢትዮጵያ ለኮቪድ እና ኤልኒኖን ጨምሮ ለዓለም የኢኮኖሚ እና የንግድ ስርዓት መመሰቃቀል እጅ ሳትሰጥ፤ ይልቁንም መሰል ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ወደ ዕድል በመቀየር፤ ለችግሮች የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ባከናወነቻቸው ተግባራት ጽናትን ገንዘቧ እያደረገች ትገኛለች።
ለዚህም ነው "አካታች ዓለም አቀፍ አስተዳደር እና ባለ ብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር” በሚል አጀንዳ ላይ ትኩረት ባደረገው የጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ችግሮች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ ጽናትን ማጠናከር እና የአስተዳደር ስርዓት አካል የማድረግን መሠረታዊ ጠቀሜታ የገለጹት። ይህ ጽኑ ስርዓት ግንባታ ኢትዮጵያ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንድትበረታ ማስቻሉን ለማሳያነት አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ ከሚገባ የስንዴ ጥገኝነት ተላቃ በምግብ ራሷን መቻሏን አንስተዋል። በጤና ቅድመ መከላከል ፖሊሲ አካል ሆኖ የሕክምና ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች ማምረትን፣ የዲጂታል ስርዓት ሽግግርንና ደኅንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀም የማስፈን አበይት ተግባራት መከናወናቸውን ነው አጽንኦት የሰጡት።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የጀመረችው የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ የነገውን የቴክኖሎጂ ዘመን በባለቤትነት እንድትመራ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን የገለጹት። በእነዚህና መሰል የልማት ትብብሮች ከጥምረቱ አባል ሀገራት ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም ነው ያረጋገጡት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ጥምረቱ የተቋቋመበትን ዓላማ እና መርህ በተጨባጭ እውን እያደረገች እንደምትገኝ በመጠቆም፤ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ስርዓት ማሻሻያ ባከናወነቻቸው አመርቂ ትግበራዎች፣ በታዳሽ ኃይል መስፋፋት እና የኢንዱስትሪ መሠረት ልማቶቿ፣ በግብርና ስርዓት ማሻሻያ እየተመዘገቡ ያሉ የምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ብሎም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ የአየር መንገድ ግንባታ የአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ንግድ ትሥሥርን ለማስፋፋት በምታደርገው ጥረት በጥምረቱ ለሚነሱ ተያያዥ የውይይት አጀንዳዎች መሪ ተዋናይ መሆን እንደሚያስችላትም አንስተዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የልዑክ ቡድናቸው የብሪክስ ጉባኤ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑ እሙን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው እያደረጉት ካለው ተሳትፎ ጎን ለጎን ቀጣናዊና ዓለም አቀፍ ትብብሮችን በሚያጠናክሩ አጀንዳዎች ላይ ከተለያዩ የብሪክስ ስብስብ አባል ሀገራት መሪዎች ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርገዋል።
በዚህም ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ ከቪየትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ሌ ሚን ሁንግ፣ ከካዛኪስታን ፕሬዚዳንት ቃሲም ጆማርት ቶካዬቭ፣ ከአቡ ዳቢ አልጋ ወራሽ ከልዑል ሼህ ኻሊድ ቢን ሙሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያ፣ ከማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም፣ ከኢራኑ ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያ እንዲሁም ከሌሎች መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ትብብርን በሚያጠናክሩ አጀንዳዎች ላይ ውጤታማ ውይይቶችን አካሂደዋል።
የውይይቶቹ ማጠንጠኛም የጥምረቱን አባል ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያበረታቱ እንደ ኢንቨስትመንት፣ ቀጣናዊ ጉዳዮች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታና ክህሎት፣ ቱሪዝም፣ የማዕድን ልማት እና ወደ ኮፕ 32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮች ላይ ያተኮሩ እንደነበሩ ተመላክቷል።