ከታሪክ ዘካሪነት ወደ ታሪክ ሰሪነት፤ የአዲሱ ትውልድ የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ አብዮት - ኢዜአ አማርኛ
ከታሪክ ዘካሪነት ወደ ታሪክ ሰሪነት፤ የአዲሱ ትውልድ የሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ አብዮት
የአንድ ሕዝብ የነፃነት ድል የሚያበቃው በድል ማግስት በሚተረክ የታሪክ መዛግብት ብቻ አይደለም። በሌላ የታሪክ ገጽ ላይ አዲስ ድል መጎናፀፍ ሲቻል የቀደመውን ድል ትርጉምና ምልዑነት የበለጠ ያጎላዋል።
ዓድዋ የክንደ ብርቱ ቅድመ አያቶች የሀገርን ሉዓላዊ ነፃነት የማስጠበቅ አኩሪ የድል ምልክት ነው። የድል ምልክትነቱም ለጭቁኑ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ፅናትና የነፃነት ጎህን በመቅደድ፣ ለአሁኑ ትውልድ ደግሞ የይቻላል መንፈስን አጎናፅፏል።
ጀግንነትንና አልበገር ባይነትን ከቅድመ አያቶቹ የወረሰው የአሁኑ ትውልድም በሌላ የታሪክ ገጽ በጉባ ተራሮች ግርጌ በዓባይ የዘመናት ዥረት ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገንባት የራሱን ታሪክ ጽፏል።
የሕዳሴ ምረቃ የተበሰረባት ጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ዕለትም የኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌትነት የሚበይኑ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች የተበሰሩባት ድርብ ታሪካዊት ዕለት ሆና ተመዝግባለች።
በሕዳሴ የይቻላል መንፈስን የተጎናፀፈችው ኢትዮጵያም በኃይል፣ በግብርና፣ በአቪዬሽን፣ በጋዝ፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች ወደ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ተሸጋግራለች።
የጉባ ብስራቶችም የአንድ ፕሮጀክት ወይም ዘርፍ ስኬት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ሀብቷን በራሷ አቅም በማልማት የብልፅግና ጉዞዋን ለማስፋት የምታደርገው የልማት ጉዞ ሕያው ምልክት ናቸው።
የመደመር መንግሥት አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ኢትዮጵያን በራሷ ልጆች የመቅረጽ ራዕይም ከዓድዋ ነፃነትን፣ ከሕዳሴ የልማት ድልን፣ ከጉባ ተራሮች ግርጌ ብስራትን በመሰነቅ ታሪክን ከመዘከር ወደ አዲስ ታሪክ መጻፍ ተሸጋግሯል።
ይህም ሕዳሴ ግድብ በአንድ የታሪክ ምዕራፍ ብቻ ተከትቦ የሚቀር የትውልድ ዓርማ ሳይሆን ለሚቀጥሉት ትውልዶች የመፈጸም አቅምና የይቻላል መንፈስ የሚያስተላልፍ ቅርስ መሆኑን ያሳያል።
የአንድ ግዙፍ የትውልዱ ብሔራዊ ፕሮጀክት ምረቃም የሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶችን ውልደት በማብሰር ኢትዮጵያ በአዲስ የስኬት ምዕራፍ እየተስፈነጠረች መሆኗን ያመላክታል።
የጉባ ብስራት የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ፣ የጋዝ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንዲሁም የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አብነቶች ናቸው።
ኃይልን ከግብርና፣ ኢንዱስትሪን ከአቬየሽን ያሰናሰሉት የጉባ ብስራት ግዙፍ ፕሮጀክቶችም በዚህ የልማት ጉዞ ቀጣዩን ምዕራፍ መጻፍ ጀምረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የምታልም ሀገር ብቻ ሳትሆን የመፈጸም አቅም ያላት መሆኗን የሚያሳይ አዲስ የልማት ምዕራፍ ነው።
በመደመር መንግሥት ውልደት ማግስት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ያስመዘገበቻቸው እመርታዎች ሀገርን ከመዋቅራዊ ስብራት ወደ ማንሰራራት ያሸጋገሩ ድሎች ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ታሪካዊቷ ዕለት እንዳሉት፤ ሕዳሴ ያስገኘው ወኔና ተስፋ የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ አድማስ የሚያበስሩ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም መንገድ ከፍቷል።
በዚህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ለሰላማዊ ዓላማ የሚውል የኒውክሌር ፕላንት፣ የጋዝ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡ ማብሰራቸው ይታወሳል።
እነዚህ ግዙፍ የልማት ዕቅዶች በቁጥር የሚገለጹ ፕሮጀክቶች ብቻ አይደሉም። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ከራሷ የመፈጸም አቅም ጋር በማሰናሰል የነገን ሀገራዊ ተስፋ የሚያመላክቱ የልማት አቅጣጫዎች ናቸው።
የመደመር መንግሥት ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ትልሞችም የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ የማንሰራራት ምዕራፍ በማብሰር፣ የሀገርን ብልፅግና የሚቀርጹ እመርታዎች የተገኙባቸው ናቸው።
ከእነዚህ መካከል የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ የፕሮጀክት ግንባታ ብስራት አንዱ ነው።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ያላትን አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በማጎልበት፣ በኢኮኖሚ፣ በቱሪዝምና በዲፕሎማሲ ዘርፎች አዳዲስ ዕድሎችን የሚከፍት ቁልፍ መሠረተ ልማት ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፕሮጀክቱን ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ነው።
በዚህ መነፅር ሲታይም የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያ ፕሮጀክት የአቪዬሽን ፕሮጀክት ብቻ አይሆንም። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላትን የአቪዬሽን መሪነት በማላቅ፣ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ይሆናል።
የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ግዝፈትና ዝማኔ ኢትዮጵያን የአቪዬሽን፣ የቱሪዝምና የዲፕሎማሲ ማዕከል የማድረግ ከፍተኛ አቅም አለው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ናቸው።
ይህም ሕዳሴ ግድብ ያስተዋወቀው የታላቅ ሀገር ግዙፍ ፕሮጀክትን የመፈጸም ባህል ከኃይል ዘርፍ ወደ አቪዬሽንና ሌሎች ስትራቴጂካዊ የልማት መስኮች እየተስፋፋ መሆኑን ያመላክታል።
ሌላኛው የኢትዮጵያን የማንሰራራት አቅጣጫ የሚበይነው ግዙፍ ፕሮጀክትም የተፈጥሮ ጋዝና የአፈር ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ የማምረት ትልም ነው።
የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ከመሬት ሥር ተደብቆ የሚቀር ሳይሆን፣ የምርት፣ የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ ልማት መሠረት የማድረግ አዲስ የዕድገት አቅጣጫ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክትን ባስጀመሩበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ የጋዝ ምርት ፕሮጀክት የኃይል አቅርቦትን ከግብርና ምርታማነት ጋር ያሰናሰለ ነው ብለዋል።
ይህም የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ የኃይል አቅርቦትን ከማሟላት ባሻገር፣ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጉዞ በስፍራው ለሚገነባው የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግብዓትነት ያገለግላል።
በዚህ አተያይም ጋዝን ማልማት የኃይል ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር፣ የግብርና ምርታማነትን፣ የኢንዱስትሪ ምርትንና የሀገር ውስጥ ግብዓት አቅርቦትን የሚያጠናክር የተሰናሰለ ስልታዊ የልማት አቅም ይፈጥራል።
የመደመር መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለብዝኅ ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት የሰጠው ትኩረትም ኢትዮጵያን በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ዘርፎች በስኬት ምሕዋር እንድትገባ አድርጓታል።
ይህም የኢትዮጵያን ማዕድን ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወደ እሴት የታከለበትና ፈጠራ ያለበት የምርት ሰንሰለት የሚሸጋገርበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ፣ የካሉብ ፋብሪካ የተፈጥሮ ጋዝ ማጣራትና ወደ ፈሳሽነት የመቀየር የማዕድን ልማት ለተሽከርካሪና ፋብሪካ አማራጭ የኃይል ምንጭ ማቅረብ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ይህ ተፈጥሮ ሀብትን በጥሬ ዕቃነት ከመሸጥ ይልቅ በማቀነባበርና በማልማት የበለጠ እሴት ለማስገኘት የተያዘውን አቅጣጫ ያመላክታል።
የመደመር መንግሥት ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የግሉን ዘርፍ በማሳተፍና ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችን በመሳብ፣ አዳዲስ የልማትና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ከፍቷል።
ለዚህም ነው የዳንጎቴ ግሩፕ ባለቤትና መሥራች አሊኮ ዳንጎቴ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም በኢኮኖሚው ውስጥ ጤናማ ውድድርና ቀልጣፋ አሠራር እንዲፈጠር አድርጓል ብለዋል።
ከሕዳሴ ግድብ እስከ አቪዬሽን፣ ከተፈጥሮ ጋዝ እስከ ማዳበሪያ ድረስ ገሃድ የገለጠው የኢትዮጵያ ማንሰራራትም ከማለም ወደ መፈጸም፣ ከመፈጸምም ወደ ዘላቂ የልማት አቅም ለመሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ ያመላክታል።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያንን አንድነትና የጋራ አቅም ለዓለም ታሪክ ያሳየ ድል እንደነበር ሁሉ፣ ሕዳሴ ግድብም ያንኑ የጋራ አቅም በዘመናዊ ልማት ላይ የገለጠ አዲስ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል።
የኢትዮጵያውያን አንድነት የዓድዋን ድል ካቀዳጀ፣ ያው በሕብር የተሸመነ አንድነትም ሕዳሴን እውን አድርጓል። ሕዳሴ የተስፋ ብርሃን ካበራ፣ ያ ተስፋም በሌሎች የልማት ሜጋ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሆኖ እየቀጠለ ነው።
ይህ የይቻላል መንፈስ ከፕሮጀክት ወደ ፕሮጀክት የሚጓዝ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ስለነገ ሀገራቸው ያላቸውን እምነት የሚያድስ የልማት ብስራት ነው።
ሕዳሴ ግድብ የተጀመረውን የተስፋ ጉዞ አዲስ አቅጣጫ አስይዞታል። የሚቀጥለው ታላቅ ተግባር ደግሞ ይህን የመፈጸም አቅም ወደ ዘላቂ ምርታማነት፣ የሥራ ዕድል፣ የዜጎች ተጠቃሚነትና የተሻለ ኑሮ መቀየር ነው።
እናም የሕዳሴ ግድብ ብስራት በግድቡ የውሃ ሙሌት ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያውያን የጋራ ህልም፣ በሀገራዊ አንድነትና በመፈጸም አቅም የሚቀጥል የልማት ብስራትን ፈንጥቋል።