ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር አፍሪካ ለችግሮቿ መፍትሔ ማቅረብ እንደምትችል ማረጋገጫ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 3 /2019 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር አፍሪካ ለችግሮቿ መፍትሔ ማቅረብ እንደምትችል ማረጋገጫ መሆኑን የዘርፉ  ባለሙያዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም፣ ሥነ-ምህዳርን በመመለስና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ለአፍሪካና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አርዓያ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑንም ተናግረዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ ዮሴፍ አምሃ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ከከባቢ አየር የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመያዝ ለሥነ-ምህዳር ጥበቃ ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

መርሃ ግብሩ ለአርሶ አደሩ፣ ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብለዋል።

የፓን አፍሪካ አየር ንብረት ፍትህ ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ሚቲካ ምወንዳ (ዶ/ር)፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራት ችግራቸውን በራሳቸው አቅም ለመፍታት ሊወስዱት የሚገባ ምርጥ ተሞክሮ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ያስመዘገበችው ስኬት አፍሪካ ለችግሮቿ መፍትሔ ማቅረብ እንደምትችል ያሳየ ነው ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ የአየር ንብረት ሻምፒዮንና የአፍሪካ የግሬት ግሪን ዋል ኢኒሼቲቭ አምባሳደር ታቢ ጆዳ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በጠንካራ አመራር የታጀበ ውጤታማ ሥራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

መንግሥት ፕሮግራሙን ከንግግር ባለፈ መሬት ላይ የሚታይና ሚተረጎም ድንቅ ኢኒሼቲቭ ነው ብለዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ የአፍሪካ አየር ንብረትና ልማት ልዩ ፈንድ አስተዳዳሪ ጀምስ ኪንያንጊ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎችን በመቅረጽና በተግባር ረገድ ለአፍሪካውያን አርዓያ መሆኗን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም