ቀጥታ፡

የጭስ አልባው ኢንዱስትሪ ትንሳኤ፡ የመደመር እሳቤ ትሩፋት

ኢትዮጵያ ሺህ ዘመናትን የተሻገሩ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አስመዝግባለች።

በዓለም የሚዳሰስ ቅርስነት ዝርዝር ከሰፈሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ  ክርስቲያናት፣ የአጼ ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የአዋሽና የኦሞ ሸለቆዎች፣ የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር፣ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር፣ የራስ ዳሽንና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮችና ሌሎችም ይገኙበታል።


 

በማይዳሰስ ቅርስነት ከሰፈሩ የኢትዮጵያ ቅርሶችም የመስቀል ደመራ በዓል፣ ፊቼ-ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ ጥምቀት፣ ሹዋሊድ፣ የሶማሌ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት፣ የወላይታ ጊፋታና የመሳሰሉት ሕያው ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማኅበረሰባዊ ትውፊቶችን ያካትታሉ።

እነዚህ ኢትዮጵያውያን ለዓለም ሕዝብ ያበረከቷቸው የመስህብ ሀብቶችም ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በገጽታ ግንባታና ለአካባቢ ልማት የሚያበረክቱት ዕድል በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የመደመር መንግሥትም ይህንን የኢትዮጵያውያንን ሰፊ የቱሪዝም አቅም በመረዳት፣ ቱሪዝምን በብዝኅ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ዕይታው ውስጥ ትኩረት ከሰጣቸው የልማት መስኮች አንዱ አድርጎታል።


 

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውም ቱሪዝም ከአምስቱ የብዝኅ የኢኮኖሚ አዕማድ አንዱ እንዲሆን በመደረጉ ዘርፉ የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል።

ይህም ዘርፉ ከነበረበት ተለምዷዊና አዝጋሚ ዕድገት የሚላቀቅበትን ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፣ ነባር ቅርሶች በማደስና በመጠገን ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገርና በገበታ ለትውልድ የመስህብ መዳረሻ ልማት የቱሪዝሙን ዘርፍ ማንሰራራት ያበስሩ ፕሮጀክቶች እውን ሆነዋል።

ለአብነትም በገበታ ለሸገር በአዲስ አበባ የተገነቡ የወዳጅነት፣ አንድነትና የእንጦጦ ፓርኮች፤ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት የመዲናዋን ዓለም አቀፍ ገጽታ መቀየር ያስቻለ ምቹ ምኅዳር ፈጥረዋል።


 

በገበታ ለሀገርና ለትውልድ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክትም ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ ሐላላ ኬላ፣ ደንዲ ኢኮ ሎጂ፣ አርባ ምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት፣ ሎጎ፣ ሸበሌ ሪዞርት፣ ኒን ሊ ፓልም ሎጂ እና የመሳሰሉት እንዲገነቡ አስችሏል።

ይህም የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን የከተማና ገጠር የቱሪዝም መዳረሻ አሰናስሎ በማልማት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተውን ገንቢ ሚና መወጣት የሚችልበትን ከፍተኛ ዕድል ከፍቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በቱሪዝም ጉዳዮች ላይ ከኤንቢሲ ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች በማስፋፋትና የመዳረሻ ብዝሃነትን በማሳደግ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በተለይም ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የኢኮኖሚ መነቃቃትን በመፍጠር በሥራ ዕድል ፈጠራም ጭምር ከአምስቱ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ማሻሻዮች መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚህም የጎብኚዎች ፍሰትን በመጨመርና የቆይታ ጊዜ በማራዘም የቱሪዝም ብዝኅ እመርታዊ ውጤቶች በየአካባቢው ኢኮኖሚን በማነቃቃት የገጠርና የከተማ ልማትን ለማስተሳሰር አዲስ ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመደመር መንግሥት የቱሪዝም መዳረሻ ልማትና የቅርስ ዕድሳት ውጤታማ ሥራ የዘርፉን ዳግም ውልደት ያበሰሩ ለውጦችን አምጥቷል ብለዋል።

ይህም የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ዘመናዊና የተሰናሰለ የከተማና ገጠር የመስህብ መዳረሻና እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።


 

የቱሪዝም አስጎብኚ ድርጅቶች እንደሚሉትም፤ የኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ የመዳረሻ ልማትና የቅርስ ጥበቃ ውጤታማ ሥራ ለቱሪስቶች መዳረሻና ጉብኝት ምቹ ምኅዳርን በመፍጠር የሀገርን ገጽታ የገለጡ ናቸው።

የታላቁ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት እንቁ ሙሉጌታ እንደገለጹት፤ የቱሪዝም መሠረተ ልማት መስፋፋት የቱሪዝም ፍሰቱን በማሳደግ ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው።


 

የኤደን ላንድ ቱር ኤንድ ትራቭል ባለቤት እንዳልካቸው የምሩ፤ ለቱሪዝም ልማት የተሰጠው ትኩረት አማራጭ የመዳረሻ ስፍራዎች በማስፋፋት ለመስህብ መዳረሻ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።

የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች እንደሚሉትም፤ በኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን መጎብኘት የሚያስችሉ ውጤታማ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።


 

ከዓለም አቀፍ ጎብኝዎች መካከል ጀርመናዊው ሉካስ ኩፕፈርናጌል፤ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች የገነባቻቸው አስደማሚ የቱሪዝም መዳረሻዎች ሀገሪቱን አፍሪካዊት ግንባር ቀደም የቱሪስት ማዕከል የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።


 

 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የሀገር ውስጥ ጎብኚ ምሕረት አሰፋ በበኩላቸው፤ የለሙት የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገርን ገጽታ የቀየሩ፣ ውብ፣ ጽዱና ዓለም አቀፍ የመስህብ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በባህልና በተፈጥሮ የታደለችውን ሀብት ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅም የመቀየር ሥራ በስፋት እያከናወነች ይገኛል።

የመደመር መንግሥት ቱሪዝምን የብዝኅ የኢኮኖሚ አዕማድ አካል በማድረግ የገነባቸው ማራኪ የመዳረሻ ስፍራዎች የዘርፉን ማንሰራራት በማጽናት ለኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተውን አቅም ለማጎልበት ያለመ ነው።

ቀጣዩ የዘርፉ ጉዞም የኢትዮጵያን ቅርስና ተፈጥሯዊ ጸጋ በመጠበቅ የመዳረሻ ብዝኅነትን በማስፋፋትና የአገልግሎት ጥራትን በማሳደግ ቱሪዝምን ከተስፋ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ውጤት የሚያሻግር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም