ቀጥታ፡

የአውሮፓ ህብረትና አባል ሀገራት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርምና አካታች ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤መስከረም 3 /2019 (ኢዜአ):-የአውሮፓ ህብረትና አባል ሀገራት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሪፎርምና አካታች ልማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ገለጹ።

የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ለጀመረችው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያና ሌሎች የልማት ሥራዎች ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። 

አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ወዲህ አስደናቂ ውጤት አስመዝግባለች። 

መንግሥት የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፣ ትግበራውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን ንግድ በማስፋት አህጉራዊ አቅማቸውን እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንት እና ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት እና አባል ሀገራቱ ለኢትዮጵያ የልማት ግቦች ስኬት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፤ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በኃይል፣ በጤና እና በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዘርፎች የላቀ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ፣ የትብብር እና የፖሊሲ ዋና ማዕከል መሆኗን ጠቅሰው፤ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋንም አንስተዋል። 

የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ በጠንካራ እና አስተማማኝ አጋርነት ላይ የተመሰረተ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ለዚህም ህብረቱና አባል ሀገራቱ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም