ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና እስራኤል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጎልበት ምቹ ምኅዳር ፈጥሯል - አምባሳደር አብርሃም ንጉሤ (ዶ/ር) 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3 /2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያና እስራኤል ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብርን ለማጎልበት ምቹ ምኅዳር መፍጠሩን በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

አምባሳደር አብርሃም ንጉሤ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት ታሪክን ከዘመናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር ጋር በማሰናሰል በሁሉም መስክ እየጎለበተ የመጣ ነው። 

በአሁኑ ወቅትም በመንግሥት ለመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ የልማት ድርጅቶች አጋርነት በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ትብብር መፈጠሩን ገልጸዋል። 

ይህም የሀገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በማጎልበት በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ የትብብር መስኮችን በማስፋት የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት አስቻይ ምህዳር መፍጠሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና እስራኤል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የእርስ በእርስ ይፋዊ የሥራ ጉብኝትም የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት መግባባትን በመፍጠር ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል። 

የእስራኤል በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አመልክተው፤ ከነዚህ መካከል በጤናው ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የልምድ ልውውጥ በማድረግና በተለያዩ መስኮች ላይ የሙያተኞችን አቅም በሥልጠና በማብቃት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር ተችሏልም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ከ100 በላይ የሚሆኑ የእስራኤል ኩባንያዎች በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች ተሰማርተው እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ለእስራኤል የምሥራቅ አፍሪካ ቁርጠኛ አጋር እንደሆነች ሁሉ እስራኤልም ለኢትዮጵያ የመካከለኛው ምስራቅ ቁርጠኛ ወዳጅ መሆኗን አስረድተዋል። 

የሀገራቱን የጋራ ተጠቃሚነት ለማላቅ በሚደረገው ጥረትም የኢትዮጵያ አየር መንገድና የእስራኤል የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ቁልፍ ሚና እየተወጡ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 

ከአዲስ አበባ እስከ ቴል አቪቭ የአራት ሰዓታት የቀጥታ በረራ ብቻ የሚወስድ መሆኑም የእርስ በእርስ የንግድና አገልግሎት ልውውጡን በአጭር ሰዓታት ለማሳለጥ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን አብራርተዋል።

ይህም እስራኤል የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን ኢትዮጵያ ደግሞ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በወጪና ገቢ የንግድ ልውውጥ እንዲሳለጥ በማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ መመስረት፣ አዲስ አበባ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ የፖለቲካል ዲፕሎማሲ ማዕከል ሀገር መሆኗም እስራኤል ለኢንቨስትመንት የምትመርጣት ሀገር እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና የዲጂታል ልማት የእስራኤል ባለሀብቶች በተለያዩ የንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች መዋለ ነዋያቸውን የሚያፈሱበትን ምቹ መደላድል እንደፈጠረ ገልጸዋል። 

ይህም እስራኤል የኢትዮጵያ የግብርና ምርቶችን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ የፈጠራና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በወጪና ገቢ የንግድ ልውውጥ እንዲሳለጥ በማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም