ሀገራዊ ምክክሩ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና መልካም ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ አዲስ ምዕራፍ የከፈተና መልካም ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው
አዳማ፤መስከረም 3/2019(ኢዜአ)፡-ሀገራዊ ምክክሩ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ከመሆኑም በላይ መልካም ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።
ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ሀገራዊ ልዩነቶችን፣ የፖለቲካ አለመግባባቶችን እና ውስብስብ የታሪክ ውዝግቦችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለመውን የሀገራዊ ምክክር አካሄዳለች።
ሂደቱም ለጋራ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና መልካም ተሞክሮ የሚወሰድበት ሆኖ ተጠናቋል።
የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ ዜጎች ችግሮቻቸውን በአፈሙዝ ከመፍታት ይልቅ ተመካክረው ልዩነታቸውን በማጥበብ ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር በየነ ደሳላኝ በሰጡት አስተያየት ሀገራዊ ምክክሩ የህዝብ ውክልና ያላቸው አካላት በጋራ ሆነው በሀገራዊ ችግሮች ላይ በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ተወያይተው በስኬት ማጠናቀቃቸው አስደሳችና የሚያኮራ ተግባር ነው።
ሀገራዊ ምክክሩ የተሳካለት ተልእኮ ነው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው በተለይ አስቸጋሪ፣ ውስብስብ እና ግራ የሚያጋቡ ሀሳቦችን ጭምር ወደ አንድ መድረክ በማምጣት ዘላቂ መፍትሄ ይሰጣል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውን አውስተዋል።
ምክክር ማለት ክርክር አይደለም ያሉት ፓስተር በየነ፤ ይልቁንስ ለችግሮቻችን እልባት ለመስጠት ሁሉንም አካል የሚያግባባ እና የመፍትሄ ሀሳብ የሚፈልቅበት መድረክ መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም በምክክሩ የተደረሰበት አጀንዳ በቀጣይ ጊዜያት ወደ ተግባር ሲቀየር የህዝቦችን ዘመናት የተሻገረ ችግር የሚገታ ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል አብራርተዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚና የኦሮሚያ ክልል አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተሰማ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን እንዲሁም ትጥቅ ፈትተው በሰላም የተመለሱ አካላትን ጭምር ባሳተፈና ባካተተ መልኩ መካሄዱ የህዝብን አመኔታ ያጎናጸፈና ለሀገሪቱ ብሩህ ተስፋን የሚፈነጥቅ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በምክከሩ የሁሉም የሀሳብ ልእልና በሚገባ የተንጸባረቀበት በመሆኑም በሀገራዊ አጀንዳ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።
ይህም በሀገሪቱ የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ከመገንባት ባለፈ ለሌላው ዓለም ምርጥ ተሞክሮና በተምሳሌትነት የሚጠቀስ እንደሚያደርገው አውስተዋል።
በአጠቃላይ በሰላም፣ ፍትሕ፣ የሕግ የበላይነት፣ እኩልነትና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በሰፊው የተመከረበት ሁነኛ ምክክር በመሆኑ ለሀገራዊ አጀንዳ ዘላቂ መፍትሄ ይዞ ይመጣል ነው ያሉት።
በኢዜማ የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተባባሪ ወይዘሮ ሠናይት በላይ በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ ዕርቅን ለማውረድ እና ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከርና ለማጽናት ምትክ የለሽ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ምክክሩ ከዚህ በፊት መንግሥትን ለመቃወም አፈሙዝ የመጀመሪያ አማራጭ ተደርጎ ሲወሰድ የነበረውን የዘመናት ልምምድ በመግታት ለችግሮች መንስዔ ለሆኑ ጉዳዮቻችን ሁሉ የውይይት ባሕልን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት አዲስ ምእራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ፍጹም ገለልተኛ ሆኖ መካሄዱን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ ይህም ዜጎች የጋራ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች በጥልቀት ተመካክረው ይበጃል ያሉትን ምክረ ሀሳብ በማስቀመጥ ስኬታማ ሀገራዊ ምክክር ማካሄዳቸው ለመጪው ትውልድ ብሩህ ተስፋን ያንጸባርቃል ባይ ናቸው ።