199ኛው የማንችስተር ደርቢ - ኢዜአ አማርኛ
199ኛው የማንችስተር ደርቢ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2019 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ማንችስተር ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ ዛሬ የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።
ጨዋታው ምሽት 12 ሰዓት ከ30 ላይ በኦልድትራፎርድ ስታዲየም ይካሄዳል።
ማንችስተር ዩናይትድ በአራት ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ በዘጠኝ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ199ኛ ጊዜ ነው።
ቡድኖቹ ከዚህ በፊት ባደረጓቸው 198 ጨዋታዎች ማንችስተር ዩናይትድ 81 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ 63 ጊዜ ሲያሸንፍ 54 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ 58 ጊዜ ተገናኝተው ማንችስተር ዩናይትድ 27 ጊዜ ሲያሸንፍ ሲቲ በ21ዱ ድል ቀንቶታል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ሁለቱም ክለቦች በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ እና ማንችስተር ሲቲ የአንድ ከተማ ባላንጣ ቡድኖች ናቸው።
ክለቦቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ1881 ነበር። በዚህ ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ 3 ለ 0 አሸንፏል።
ቡድኖቹ ከመጀመሪያ ጨዋታቸው አንስቶ ለ145 ዓመታት የቆየ ፉክክር በእንግሊዝ እና በአውሮፓ መድረክ አድርገዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ የሊጉን ዋንጫ 20 ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዟል። ማንችስተር ሲቲ 10 ጊዜ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል።
ሁለቱ ክለቦች በፕሪሚየር ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የተጋናኙት በጥር ወር 2018 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ ማንችስተር ዩናይትድ 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ማንችስተር ዩናይትድ በሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ከኤቨርተን ጋር ሁለት አቻ ተለያይቷል። በጨዋታው ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
የከተማ ተቀናቃኙ ማንችስተር ሲቲ በሶስቱም የሊጉ ጨዋታዎች አሸንፏል። ዛሬ ድል ቀናው የሊጉን መሪነት ከአርሰናል በድጋሚ የመረከብ እድል አለው።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የ41 ዓመቱ ማይክል ኦሊቨር ተጠባቂውን የደርቢ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በዕለቱ ሌላኛው መርሐ ግብር ኮቨንተሪ ሲቲ ከብራይተን በኮቨንተሪ ቢውልዲንግ ሶሳይቲ አሬና ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።