18ተኛ የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ - ኢዜአ አማርኛ
18ተኛ የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በ18ተኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደ ሕንድ ኒው ዴልሂ አቅንተው፣ ዛሬ መስከረም 2 ቀን፣ 2019 ዓ.ም ‘‘ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት’’ በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ በዋለው የመሪዎች ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል።
ጉባኤው በመጀመሪያ ቀን ውሎ “አካታች ዓለም አቀፍ አስተዳደር እና ባለ ብዙ ወገን ትብብርን ማጠናከር” በሚል ዓቢይ ጉዳይ ላይ የተወያየ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ አስተዳደር አካታችና ሚዛናዊ የሆነ የሀገራት ተሳትፎ ብሎም ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በተያያዘም ከተመሰረት 20ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ይህ ጥምረት በሚቀጥሉት ዓመታት ይበልጥ የተደራጀ፣ ባለብዙ ወገን ትብብሮችን ያጠናከረ፣ ፍትሃዊ፣ አሳታፊና አካታች የሆነ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ እንዲሆን ይበልጥ እንደሚሰራ ተመላክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጉባኤው ባደረጉት ንግግርም፣ ችግሮች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ ጽናትን ማጠናከር እና የአስተዳደር ስርዓት አካል የማድረግን መሰረታዊነት አመላክተው ይህ ጽኑ ስርዓት ግንባታ ኢትዮጵያ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ እንድትበረታ እንዳደረጋት ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አክለውም በምግብ ከውጭ ከሚገባ የስንዴ ጥገኝነት ተላቃ ራሷን መቻሏ፣ በጤና ቅድመ መከላከል ፖሊሲ አካል ሆኖ የህክምና ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች ማምረትን፣ የዲጂታል ስርዓት ሽግግርንና ደኅንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀምን፣ የአኅጉሪቱን የጥናትና ምርምር ብሎም ፈጠራ አዳጊ ፍላጎት ሊያሳካ የሚችል የመደመር ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታን የጠቆሙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በእነዚህና መሰል የልማት ትብብሮችም ከጥምረቱ አባል ሀገራት ጋር አብሮ ለመስራት ያላትን ተነሳሽነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2027 COP 32 ጉባኤን በአዲስ አበባ ለማስተናገድ የተጣለባትን ኃላፊነት በተግባርና በተስፋ እንደምትወጣው በመግለጽ፣ እስከ COP 32 ድረስ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ወደ ስምምነት የሚቀይር "የብሪክስ አስተባባሪ መስመር" እንዲቋቋም ሃሳብ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ ለዚህ አጋርነት የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
ከመሪዎቹ ጉባኤ ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአባል ሀገራቱና አጋር ሀገራት መሪዎች ጋር በሁለትዮሽ የሀገራቱ ትብብር ዙሪያ ፍሬያማ ውይይቶችን ያካሄዱ ሲሆን፤ በኢንቨስትመንት፣ ቀጣናዊ ጉዳዩች፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታና ክህሎት፣ ቱሪዝም፣ የማዕድን ልማት እና ወደ ኮፕ 32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉ ትብብሮች በጥልቀት ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ስርዓት ማሻሻያ ባካሄደችው አመርቂ ትግበራዎች፣ በታዳሽ ሀይል መስፋፋት እና የኢንዱስትሪ መሠረት ልማቶቿ፣ በግብርና ስርዓት ማሻሻያ እየተመዘገቡ ያሉ የምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ብሎም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ የአየር መንገድ ግንባታ የአኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ንግድ ትሥሥርን ለማስፋፋት በምታደርገው ጥረት በጥምረቱ ለሚነሱ ተያያዥ የውይይት አጀንዳዎች መሪ ተዋናይ እንድትሆን ያስችላታል።
#PMOEthiopia