ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ፍትሃዊ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ፍትሃዊ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ):- በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ፍትሃዊና ተደማጭነታቸውን ያረጋገጠ ውክልና ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ዛሬ በህንድ ኒው ዴልሂ መካሄድ ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር የማዕድን ሀብት ለኢነርጂ ሽግግር፣ ለላቀ ማኑፋክቸሪንግ እና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካ የበርካታ ማዕድናት ሀብት ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፤ የብሪክስ አባል ሀገራት ደግሞ የካፒታል፣ የቴክኖሎጂ እና የገበያ አማራጭ እንዳላቸው አንስተዋል።
እነዚህን ሀብቶች አቀናጅቶ ለመጠቀምና በጥሬ ሃብቱ ላይ እሴት ለመጨመር የብሪክስ ጥምረት ትልቅ እድልን የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በማዕድናት፣ በታዳሽ ኢነርጂ እና እያደገ ያለውን የኢንዱስትሪ አቅሟን መሰረት ባደረገ መልኩ አጋርነቶችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ትስስር ያላት አበርክቶ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከዓለም ጋር እያገናኘ እንደሚገኝ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገራቱ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስ እና የአፍሪካ ህብረት ያላቸው ትብብር ከአጀንዳ 2063 ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ድጋፏን እንደምትሰጥም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ጋር በተያያዘ ባነሱት ሀሳብ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማድረጓን እና የውጭ ዕዳዋን ለማሸጋሸግ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
በፈተና ውስጥ ለሚገኙ ኢኮኖሚዎች ጊዜ ውድ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው፤ የዕዳ አከፋፈል ሂደት ፈጣን፣ ግልጽ እና ተገማች መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ሀገራት በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ያላቸው ውክልና ፍትሃዊ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ውክልናው ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።