ቀጥታ፡

የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ አፍሪካ የነገውን የቴክኖሎጂ ዘመን በባለቤትነት እንድትመራ ትልቅ ሚና ይጫወታል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ):- አፍሪካ የነገውን የቴክኖሎጂ ዘመን በባለቤትነት እንድትመራ የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ዛሬ በህንድ ኒው ዴልሂ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ዓለም አቀፍ ቀውሶች የሚያስከትሉት ጉዳት በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ሳይወሰኑ ተደራራቢ መስተጓጎል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

ሀገራት ቀውሶች ከመከሰታቸው በፊት የመቋቋም አቅም ሊገነቡ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ ፈተናን መቋቋም የሚያስችሉ ስርዓቶችን እየገነባች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

መንግስት በምግብ ዋስትና ላይ ባከናወነው ተግባር ኢትዮጵያ ከውጭ ከሚገባ ስንዴ ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ወጥታ ራሷን መቻሏን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ሀገሪቱ ለታቀደው የብሪክስ የሰብል ልውውጥ ማዕቀፍ (BRICS Grain Exchange) እንደ አምራችም ሆነ አቅራቢ ሆና ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

በጤናው ዘርፍም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ትልቅ ትምህርት መስጠቱን ነው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ቀውሶችን ለመቋቋም የሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን እያሳደገች እንደምትገኝ ገልጸው፤ የፋርማሲዩቲካልና የመድኃኒት ማምረቻዎችንም እያስፋፋች መሆኗን ጠቁመዋል።

በቴክኖሎጂው ዘርፍ ዲጂታል መሠረተ ልማት፣ ዲጂታል መታወቂያ (Digital ID)፣ የክፍያ ሥርዓቶች እና የመረጃ ልውውጥ በስፋት እየተገነቡ መሆናቸውን አንስተዋል።

መረጃዎች ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ በሕግ አግባብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ይህንን ለውጥ የበለጠ እንደሚያጠናክረው አመልክተዋል።

በቀጣዩ ትውልድ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ይበልጥ ሰዎችን ማገልገል፣ ብዙ ቋንቋዎችን መረዳት እና ሰፊ የሰው ልጅ እውቀት ማካተት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል።

አፍሪካ የነገውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘመን በባለቤትነት ለመምራት የምርምር፣ የኮምፒውቲንግ አቅም፣ ክህሎት እና ተቋማት እንደሚያስፈልጋት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችውም የመደመር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም አፍሪካ የወጠነችውን ግብ የማሳካት አላማ እንዳለው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካን የሚወክል የቴክኖሎጂ አቅም ለመገንባት ከብሪክስ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላትም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሰዎችን ማዕከል ያደረገ የኤአይ አስተዳደር መደገፍ እንዳለበት እና ጥሩ አስተዳደር ከብቃት ጋር ሊጣጣም እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም