ቀጥታ፡

የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የዲጂታል ግብር ክፍያ ሥርዓት ጀመረ

ሰመራ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦የአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር የዲጂታል ግብር ክፍያ ሥርዓት ጀመረ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሰመራ ሎጊያ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ ኑርሳሊም፤ የዲጂታል የግብር ክፍያ ሥርዓት ቀልጣፋ አሰራርን ከመዘርጋት ባለፈ ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የሚያስችል ዘመናዊ አሰራር መሆኑን ገልጸዋል።


 

የግብር አሰባሰብ ሂደቱ ለብልሹ አሰራር እንዳይጋለጥ እና የግብር መሰወር ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችል ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ግብር ከፋዮች ምንም አይነት እንግልት ሳይገጥማቸው ባሉበት ሆነው የሚከፍሉበት ስርአት መዘርጋቱ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።

ግብር ከፋዮች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በቴሌብር አማራጮች ባሉበት ሆነው ግብራቸውን በመክፈል ከእንግልት በጸዳ መልኩ ሃላፊነታቸውን በቀላሉ መወጣት ያስችላቸዋል ብለዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ ኡመር ኑር እና ሌሎችም የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም