በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ እየተከናወነ ያለው ልማት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ እየተከናወነ ያለው ልማት በትምህርት ተደራሽነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው
ነገሌ ቦረና ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ እየተከናወነ ያለው ልማት በጥራትና ተደራሽነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን የዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
በዞኑ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪ ክፍል ጥምርታን ለማመጣጠን 18 ቅድመ መደበኛ እና አምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ቦረና ዞን የትምህርት ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ዲዳ ገልገሎ፤ በአዲሱ ዓመት ለትምህርት የተደረገውን ዝግጅት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም ለትምህርት ሴክተሩና አጠቃላይ ለመማር ማስተማሩ ሂደት በተለይም ለትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በመሆኑም በአዲሱ የትምህርት ዘመን ከ189 ሺህ 340 በላይ መደበኛ ተማሪዎችን ለመቀበል የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ለአዲሱ የትምህርት ዘመን የተማሪ ክፍል ጥምርታን ለማመጣጠን 18 ቅድመ መደበኛ እና አምስት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የትምህርት ቤቶቹ መገንባት በ2019 የትምህርት ዘመን ከ1 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በድምሩ ምስራቅ ቦረና ዞን በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ እየተከናወነ ያለው ልማት በጥራትና ተደራሽነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ይገኛል ብለዋል።
የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ኑራ አብዱባ፤ በመንግስት ለትምህርት ሴክተሩ የተሰጠው ትኩረት ልጆቻችን የተሻለ የትምህርት እድል እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት በተጨማሪ የቆዩ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተደረገው የልማት ስራ የሁላችንም ተሳትፎ ተጨምሮበት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ አስደስቶናል ብለዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ መቶ አለቃ አማረ አስራት፤ የትምህርት ቤት ግንባታ የትውልድ ግንባታ መሰረት በመሆኑ የሁላችንም ተሳትፎ የግድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በህዝቡና በመንግስት ጠንካራ ትብብርም በዞኑ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና አዲስ በመገንባት ለመማር ማስተማሩ ዝግጁ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት በተጨማሪ ለግብአት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ በንቃት መሳተፋቸውን አንስተው ጥረታችን ይቀጥላል ብለዋል።