በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት በሚል መሪ ቃል በሕንድ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ አካል በመሆናችን ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለው መልካም ዕድል እነዚህን አቅሞች በማስተሳሰር የላቀ እሴት መፍጠር እና ይህ እሴት ደግሞ ሀብቱ በሚገኝበት ቦታ መመረት እንዲችል ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በማዕድን ልማት፣ በታዳሽ ኃይል እና እያደገ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መሠረቷ ላይ እነዚህን አጋርነቶች ለመገንባት ዝግጁ ናትም ብለዋል።
በተጨማሪም በአሠራር ሥርዓቶቻችን ውስጥ ጽናትን መገንባት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የአህጉራችንን ፍላጎት እንዲያገለግል ማድረግ፣ አስተማማኝ የዕዳ እፎይታ ሒደትን ማሳደግ እንዲሁም የአየር ንብረት ጥበቃ ሥራዎችን ከኢኮኖሚ ሽግግር ጋር ማስተሳሰር ይኖርብናል ሲሉም ገልጸዋል።
የብሪክስ መድረክ የጋራ ትብብርን ወደ የጋራ እሴት፣ ጽናት እና ዘላቂ ዕድገት የመለወጥ ሰፊ አቅምና ቁርጠኝነት እንዳለውም ነው ያመላከቱት።