ቀጥታ፡

በትምህርት ዘርፍ የተወሰዱ ውጤታማ የማሻሻያ እርምጃዎች በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦በትምህርት ዘርፍ የተወሰዱ ውጤታማ የማሻሻያ እርምጃዎች በትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ መንግሥት የተሟላ ዜጋ የማፍራት፣ የግብረገብና የእውቀት መለኪያዎችን የማጠናከር እንዲሁም የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶችን የጥራት ልዩነት በማጥበብ የትምህርት አሰጣጡን ወደ ላቀ ደረጃ የማሸጋገር ሰፊ የሪፎርም ስራዎችን አከናውኗል።

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ጥራት ያለውና በእውቀት የተካነ ትውልድ ለማፍራት የተከናወኑት ስራዎች ውጤት እያሳዩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡


 

የሀገር አቀፍ ፈተናዎች ታማኝነትን ለማረጋገጥ ሲባል የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንዲሰጡ መደረጉ የትምህርት አሰጣጡን እውነተኛ ገጽታ ማሳየት ማስቻሉን ጠቁመዋል።

ከውጤት መሻሻል አንጻር በተደረጉ የማሻሻያ ተግባራትና በትምህርት ጥራት ቁጥጥር በ2018 የትምህርት ዘመን ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች ምጣኔ ወደ 12 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።

ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች በልዩ ድጋፍና ክትትል በማስተማር ለሀገር ዕድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የትምህርት ሚኒስቴር ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል። 

ሚኒስቴሩ በ2018 የትምህርት ዘመን በቦንጋ፣ በጅግጅጋ፣ በጋምቤላ፣ በወሊሶና ቡኢ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡ 

ይህንን ውጤታማ አሰራር ለማስፋት በያዘው ዕቅድ መሰረት በ2019 የትምህርት ዘመን የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ለማሳደግ በአርባ ምንጭ፣ በባህርዳር፣ በድሬዳዋ እና በአሶሳ ተማሪዎችን አወዳድሮ ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ 13 አዳዲስ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።


 

ከትምህርት ግብዓትና ቴክኖሎጂ አንጻርም የኮምፒውተር ላቦራቶሪዎችን በማስፋፋት፣ የዲጂታል መጽሐፍትንና የኢንተርኔት መሠረተ ልማቶችን ወደ ትምህርት ቤቶች በመዘርጋት የተማሪዎችን የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት የማሳደግ ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡ 

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ባለፉት 3 ዓመታት ውስጥ 146 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ሀብት በገንዘብና በዓይነት ማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ሀብት 14 ሺህ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለተማሪዎች ምቹ ሆነው መታደሳቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

በሌላ በኩል የተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ የማቋረጥ መጠንን ለመቀነስና የመማር ብቃታቸውን ለማሳደግ በተዘረጋው የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወደ ራስ ገዝነት ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ምደባም በውድድር፣ በእውቀትና በችሎታ ላይ ብቻ በተመሰረተ ግልጽ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ከተከናወኑት የሥርዓተ-ትምህርት ክለሳዎች፣ የግብረገብና የታሪክ ትምህርቶች መካተት እንዲሁም ከመዋቅራዊ ሪፎርሞች አንጻር ሀገሪቱን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ዘርፎች በብቃት ሊመሩ የሚችሉ ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ማፍራት የሚያስችል ትክክለኛ መሠረት ተጥሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም