በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀረጹት ዘርፎች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀረጹት ዘርፎች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀረጹት ዋና ዋና ዘርፎችና ሌሎችም ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዘመዴነህ ንጋቱ ገለጹ፡፡
አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባወጣው የቅርብ ጊዜ መረጃ መሰረት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከተመዘገበባቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን አንስተዋል፡፡
ይህም በሀገሪቱ ከተተገበሩት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ከተከተለችው የረጅም ጊዜ የልማት ስትራቴጂ የሚመነጭ መሆኑን አመልክተዋል።
በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተተገበረባቸው ዘርፎች ማለትም በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተመዘገቡት ውጤቶች አበረታች ናቸው ብለዋል።
በተለይም በማዕድን ዘርፍ በሀገሪቱ የታሪክ ሂደት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የወርቅ ኤክስፖርት ገቢ መመዝገቡን የጠቀሱት ባለሙያው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከወርቅ የወጪ ንግድ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉ የሪፎርሙ ትልቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የ“ኢትዮጵያ ታመርት” ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የሀገር ውስጥ ምርት አቅምን በማሳደግና የማምረት ሂደትን በማጠናከር ረገድ ከነበረበት መነሻ ተነስቶ ከፍተኛ ዕድገት ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
በግብርናው ዘርፍ ከተለመደው ባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊና ሜካናይዝድ አሰራር በመሸጋገር ቀደም ሲል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን ማስቀረት የተቻለ ሲሆን፣ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተጀመረበት አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ተናግረዋል፡፡
በቴክኖሎጂ ዘርፍ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂው ዘርፍ፣ በተለይም ለአርቲፊሻል ኢንቴሊጀንስ (AI) የሰጠችው ከፍተኛ ትኩረትና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራቷ በኦፊሴላዊ መልኩ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪና መሪ የሚያደርጋት ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፉ የገበታ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የተከናወኑት የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችና የመዳረሻ ልማት ሥራዎች የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ለኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በአገልግሎት ዘርፍ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትርፋማነቱ፣ በኔትወርክ ማስፋፋቱና በስኬታማነት መቀጠሉን ጠቅሰዋል፡፡
በፋይናንስ ዘርፉም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎች የግል ባንኮች ያስመዘገቡት በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የትርፍ መጠን በሀገሪቱ የጎላ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ለኢኮኖሚ ዕድገት ያላትን መሰረት በማጠናከር ረገድ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማትና የጋዝ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውና መጠናቀቃቸው ለኢኮኖሚው ከፍተኛ እንቅስቃሴ መፍጠራቸውን ጠቁመዋል።
ለአብነትም የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ከአምስት ሺህ ሜጋዋት ወደ 10 ሺህ ሜጋዋት ገደማ በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን አሳታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የግል ባለሀብቶች ከሀገር ውስጥ አልፈው በውጭ ሀገራት ኢንቨስት እንዲያደርጉ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ አቅሙን አጠናክሮ በመቀጠል በክልሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ጠንካራ የሚያደርጉ ግዙፍ ኩባንያዎችን መፍጠር እንደሚገባው አሳስበዋል።