በደቡብ ወሎ ዞን በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ሆነዋል
ደሴ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ) ፦ በደቡብ ወሎ ዞን የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እስካሁን ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የዜጎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ንቅናቄና ተሳትፎ ቡድን መሪ ምስጋናው ደምሴ፤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ በዞኑ በክረምቱ የተከናወኑ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ገልጸዋል።በዞኑ በክረምቱ ከ1ጥብ 2 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች ነፃ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በዚህም የቤት እድሳትና ግንባታ፣ የግብርና ስራዎችን የማገዝ፣ ለተማሪዎች የደብተርና ሌሎች ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ እንዲሁም የደም ልገሳና ሌሎችንም ማህበራዊ አገልግሎቶችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በእስካሁኑ አገልግሎታቸው ከ2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል በዞኑ ቃሉ ወረዳ የሚኖሩት አርሶ አደር ደሳለኝ አህመድ፤ ከአንድ ሄክታር በላይ መሬታቸው በበጎ ፈቃደኞች ታርሶ በዘር የተሸፈላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የእርሻ ማሳቸውን በዘር ለመሸፈን አቅመ ደካማ በመሆናቸው ይቸገሩ እንደነበር አንስተው በተደረገላቸው ድጋፍና መልካም ተግባር ለሁሉም ምስጋና አቅርበዋል።
በዞኑ ተሁለደሬ ወረዳ የሚኖሩት ወይዘሮ ሰዓዳ የሱፍ፤ የመኖሪያ ቤታቸው በእርጅና ምክንያት በተለይም በክረምት ለዝናብና ለብርድ ይዳርጋቸው እንደነበር አስታውሰው አዲስ ቤት ተሰርቶ የተሰጣቸው በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ ዓመት በተሰራላቸው ቤት አዲስ ህይወት መኖር መጀመራቸውንም ገልጸው ለበጎ አድራጊዎች ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።