ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ብራዚል የኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ወደ አዲስና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ብራዚል የኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ወደ አዲስና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ዣንዲር ፈሬራ ገለጹ፡፡ 

በኢትዮጵያ የብራዚል አምባሳደር ዣንዲር ፈሬራ ዶስ ሳንቶስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያና ብራዚል መካከል የኢኮኖሚ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የስትራቴጂካዊ ዘርፎች ያለው አጋርነት እየሰፋ መጥቷል።

በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ወደ አዲስና ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል ብለዋል።

ብራዚል በአፍሪካ የመጀመሪያውን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ኤጀንሲ (ApexBrasil) ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ የከፈተች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የፖለቲካ ትብብር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

የብራዚል ባለሀብቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድሎች እና የግል ዘርፍ አቅም እንዲረዱ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የጠበቀ የሁለትዮሽ ትብብር እንዲፈጥሩ ያመቻቻል ብለዋል።

የግብርና ዘርፍ የሁለቱም ሀገራት ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት ከሚሰሩባቸው ዋነኛ የትብብር መስኮች አንዱ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ብራዚል ኢትዮጵያ እየተገበረች ከምትገኘው የ"አረንጓዴ አሻራ" መርሃ-ግብር ትልቅ ተሞክሮ እንደምትወስድ ጠቁመዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ በሀገሪቱ የተመዘገቡ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን፣ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔን እና የመሠረተ ልማት ዕድገቶችን መታዘባቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም