ቀጥታ፡

‎‎ኢትዮጵያና ማሌዢያ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት ለመመስረት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም አላቸው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦‎‎ኢትዮጵያና ማሌዢያ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት ለመመስረት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብሪክስ ጉባኤ ጎን ለጎን ከማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

‎‎ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ በሕዳር 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ካደረጉት ታሪካዊ ጉብኝት የተገኘውን መልካም ዕድል ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተናል ብለዋል።

‎‎ውይይታቸውም ኢንቨስትመንትን፣ ቱሪዝምን፣ የታዳሽ ኃይል አጋርነትን ማስፋፋት እና ወደ ኮፕ 32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልጸዋል።

በተጨማሪም በማሌዢያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት፣ ምርታማነት እና የአምራች ዘርፍ ተሞክሮዎችን መውሰድ በሚቻልባቸው ዕድሎች ዙሪያ መምከራቸውን አስታውቀዋል።

‎‎ኢትዮጵያና ማሌዢያ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት ለመመስረት የሚያስችል ከፍተኛ አቅም አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ይህም በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ በክህሎት እና በዘላቂ ልማት ማዕቀፎች አዳዲስ ዕድሎችን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም