ቀጥታ፡

በክልሉ የወባ ወረርሽኝን ቀድሞ ለመከላከል የኬሚካል ርጭትና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የክረምት መውጣትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችል የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል የኬሚካል ርጭትና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮ የክረምት ወቅት የተስተዋለው  የዝናብ ሥርጭት መቆራረጥ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደርጋል።


 

በመሆኑም ቢሮው በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭት በስፋት ሊከሰትባቸው ይችላል ተብለው በተለዩ 17 ወረዳዎች ላይ የኬሚኬል ርጭት እያካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

የኬሚካል ‎ርጭቱ ከነሀሴ ወር 2018 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ቤት ለቤት እየተካሄደ ሲሆን ለዚህም 224 ሺህ 930 ኪሎ ግራም የፀረ ወባ ኬሚካል ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም 471 ሺህ 578 መኖሪያ ቤቶች ላይ ርጭት እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳምጤ፣ የኬሚካል ርጭት ሥራው 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚጠጉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ ይታደጋል ብለዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ ‎ከኬሚካል ርጭቱ በተጨማሪ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበረሰቡን በማስተባበር ለወባ መራቢያ አመቺ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስና የማዳፈን ሥራ ተከናውኗል።

‎ከተያዘው መስከረም ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር የወባ ትንኝ በስፋት የሚራባበት ወቅት መሆኑን አቶ ዳምጤ ገልጸው፣ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተጀመረው የኬሚካል ርጭትና የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

በክልሉ "የአርብ ጠንካራ እጆች በሽታን ይገታሉ" በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ በየሳምንቱ ይቀጥላል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከአካባቢ ቁጥጥር ሥራው ጎን ለጎን የወባ በሽታ መከላከያ አልጋ አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት ገልጸው፣  የወባ በሽታ ምልክት ሲያይም ወደጤና ተቋማት ፈጥኖ በመሄድ እንዲታከም አሳስበዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የፈገራ ወረዳ አርሶ አደር አለሙ ሙጬ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የወባ በሽታን ቀድመው ለመከላከል በቤት ውስጥ የአልጋ አጎበር ከመጠቀም ባለፈ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈንና የማፋሰስ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

የክረምት ዝናብ መቆራረጥን ተከትሎ የወባ በሽታ እንዳይቀሰቀሰ የአካባቢ ቁጥጥር ስራን በየጊዜው እያከናወኑ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደር ዳኘ ዋለ ናቸው።

‎ቀደም ሲል የተሰጣቸውን የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም ቤተሰቦቻቸውን ከወባ በሽታ መታደግ እንደቻሉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም