የኢትዮጵያና ሕንድ ግንኙነት ወደ አዲስ የታሪካዊ ትብብር ከፍታ ይሸጋገራል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሕንድ ግንኙነት ወደ አዲስ የታሪካዊ ትብብር ከፍታ ይሸጋገራል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ሕንድ ግንኙነት ወደ አዲስ የታሪካዊ ትብብር ከፍታ ይሸጋገራል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብሪክስ ጉባኤ ጎን ለጎን ከሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የሁለቱን ሀገራት አጋርነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
በውይይታቸውም የመከላከያ ትብብርን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ፣ የማዕድን ዘርፍ እንዲሁም ወደ COP32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
እነዚህ የትብብር መስኮች የተግባር ትብብርን ለማጠናከር እና ለሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች አዳዲስ እድሎችን ለመፍጠር ከፍተኛ አቅም እንዳላቸውም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እና ሕንድ ጥልቅ ታሪካዊ ግንኙነት፣ የቆየ የባህል ትስስር እና በሕዝቦቻቸው መካከል ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው ቢሆንም፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ብዙ አቅም አሁንም ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በመሆኑም የታሪክ እና የመልካም ፈቃድ ትስስሩን በቴክኖሎጂ፣ በክህሎት፣ በኢንቨስትመንት፣ በዘላቂ ልማት እና በተጠናከረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ወደተመሠረተ የበለጠ ታላቅና የጋራ ተጠቃሚነትን ወደሚያረጋግጥ አጋርነት ለመቀየር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።