ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሂላል አል-ሳሂል፤ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ መልስ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሂላል አል-ሳሂል፤ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ መልስ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2019 (ኢዜአ):- በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ቅድመ ማጣሪያ ዙር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የመልስ ጨዋታውን ዛሬ ከሱዳኑ ሂላል አል-ሳሂል ጋር ያከናውናል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይካሄዳል።
ሁለቱ ክለቦች ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሩዋንዳ በሚገኘው ኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የ2 ለ 1 ሽንፈት አስተናግዷል።
ዋሊድ አል-ሻላ እና ፋሪስ ሞሂ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል። ካርሎስ ዳምጠው ለወልዋሎ ጎሏን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ጎል አስቆጥሮ ተመልሷል።
በአህጉራዊ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ጨዋታ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የማጥቃት እንቅሰቃሴ አድርጓል።
በሁለተኛው አጋማሽ ቡድኑ በተጋጣሚው ብልጫ የተወሰደበት ሲሆን ፋሪስ ሞሂ የማሸነፊያውን ጎል ያስቆጠረው በዚሁ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነው።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ጨዋታ ከአንድና ከዚያ በላይ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሸጋግረዋል።
ቡድኑ በጨዋታው የግድ ግብ የሚያስፈልገው በመሆኑ የጎል እድሎችን በሚገባ መጠቀም ይኖርበታል።
ተጋጣሚው ሊከተለው የሚችለውን የመልሶ ማጥቃት እና የክንፍ መስመር እንቅስቃሴ መግታት ይጠበቅበታል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በሁለተኛ ዙር ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም እና ከሊቢያው አል አህሊ ትሪፖሊ አሸናፊ ጋር የሚጫወት ይሆናል።