የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች የሚፋጠኑበት ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች የሚፋጠኑበት ይሆናል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2019 (ኢዜአ)፦የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የብልፅግና ጉዞን በማስፋት የዜጎችን ሕይወት የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች የሚፋጠኑበት እንደሚሆን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን በማስመልከት በልደታ ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ማዕድ አጋርተዋል።
በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በማዕከሉ ምገባ ዘወትር የሚከናወን ቢሆንም፣ በዛሬው ዕለት በበዓሉ ምክንያት እዚህ የተገኘነው ለእናንተ ያለንን አክብሮት፣ ፍቅርና ቤተሰባዊነት ለመግለጽ ነው ብለዋል።
አዲሱ ዓመትም የበለጠ የምንደጋገፍበት፣ በአንድነት የምንበለፅግበትና የተሻለ ሕይወት የምንገነባበት ዓመት ይሁን በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
አዲሱ ዓመት የብልፅግና ጉዞን በማስፋት የዜጎችን ሕይወትና የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽሉ የልማት ሥራዎች የሚፋጠኑበት እንደሚሆን ተናግረዋል።
የ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን አስመልክቶ በተዘጋጀው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር የተሳተፉ ወገኖችም፣ ከንቲባዋ በዓሉን አብረዋቸው በማሳለፋቸው ትልቅ ክብርና ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
አስተያየት ከሰጡት መካከል አስናቀች ደቦታ እንዳሉት፣ ጧሪ ልጅ ባይኖራቸውም ከንቲባዋ ደጋፊ ሆነው ተቀብለዋቸዋል። በዓሉንም አብረዋቸው በማሳለፋቸው እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ዘሪቱ መንገሻ በበኩላቸው፣ ከንቲባዋ በዓሉን አብረዋቸው በማሳለፍ ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች ያላቸውን አክብሮትና ተቆርቋሪነት በማሳየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
በበጎነት መንደር ቤት አግኝተው የተሻለ ኑሮ መኖር በመቻላቸውና በምገባ ማዕከሉ የዕለት ጉርሳቸውን እያገኙ በመሆናቸው ለከንቲባዋና ለመንግሥት ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ ደልዩ ጫልቺሳ ቦጋለ ናቸው።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ኮሌ ፈየራ በበኩላቸው፣ በዓሉን አስመልክቶ ለተደረገላቸው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለ30 ዓመታት ያህል በጽዳት ሥራ ላይ በመሰማራት ሕይወትን ያለ ደጋፊ ስገፋ ቆይቻለሁ ያሉት ደግሞ መድህን ሀጎስ ናቸው።
አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ ቤት ሰጥቷቸው በምገባ ማዕከሉም የዕለት ጉርሳቸውን እያገኙ በመሆናቸው ምስጋና አቅርበዋል።
በበዓሉ ዕለትም ከንቲባዋ አብረዋቸው ማዕድ በመጋራታቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ግርማ ማሞ በበኩላቸው፣ በምገባ ማዕከሉ በየዕለቱ የእለት ጉርሳቸውን እንዲያገኙ ከመደረጉ ባሻገር፣ በዛሬው ዕለት በተደረገላቸው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።