የአፍሪካ የልማትና ትብብር ዓርማ - ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በታዋቂው ታይም መጽሔት ገጽ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የልማትና ትብብር ዓርማ - ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በታዋቂው ታይም መጽሔት ገጽ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2019 (ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጫነት በላይ ትርጉም ያለው፣ የአፍሪካን የውስጥ ጥንካሬ መገለጫ እና የቀጣናዊ ትብብር ማሳያ ነው።
እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆሽ ዊልሰን በታዋቂው ታይም መጽሔት “THE POWER TO UNITE AFRICA” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ጽሑፍ ላይ፣ ይህ ታላቅ ፕሮጀክት በአፍሪካ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ገልጿል።
አህጉራዊ ትስስርን የማጠናከር አቅም ያለው፣ የቴክኖሎጂን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ዕድገትን ጉዞ አሳላጭ የሆነው ይህ ግድብ፣ አስደማሚ በሆነ መልኩ መገንባቱን አመልክቷል።
ግድቡ ከተለመዱት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ከውጭ አበዳሪዎች ውጪ በኢትዮጵያውያን ብቻ መገንባቱ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አኩሪ ታሪክ ነው።
በቦንድ ግዢና በገንዘብ ድጋፍ የተከናወነው ይህ ፕሮጀክት፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን የልማት አጀንዳ በራሳቸው አቅም መደገፍ እንደሚችሉ የሚያሳይ መሆኑ ተጠቅሷል።
ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያለው የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያላይዜሽን እና የኤሌክትሪክ ፍላጎት መሟላት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የግድቡ ፋይዳ በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን፣ የኃይል አቅርቦትን ለጎረቤት አገራት ተደራሽ በማድረግ የምሥራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ገበያ የማስተሳሰር አቅም አለው።
ከሀገር ድንበር ባሻገር የሚዘረጉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች የቀጣናውን ሕዝቦች የኢኮኖሚ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ያጠናክራሉ።
የህዳሴ ግድብ ንጹህ ኢነርጂ ለቀጣናው አገራት በማቅረብ የካርቦን ልቀት እንዲቀንስ እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች እንዲጠናከሩ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ፕሮጀክት ከጂኦፖለቲካዊ ውዝግብ ማዕቀፍ ወጥቶ እንደ ሰፊ የልማት እና የትብብር ዕድል ሊወስደው እንደሚገባ ጆሽ ዊልሰን ይገልጻል።
የኢነርጂ ንግድና የጋራ የውሃ አጠቃቀም ስምምነቶች ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንደሚፈጥሩ ሳይንሳዊ ጥናቶችን አብነት በማድረግ ጸሐፊው አስቀምጧል።
የውሃ ፍሰት አስተዳደርን ከኤሌክትሪክ ንግድ ጋር መተሳሰሩ በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ አገሮችን የውሃ አቅርቦት ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ የጋራ ዕድገትን እውን እንደሚያደርግ አመልክቷል።
ግድቡ በረጅም ጊዜ የድርቅ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጋራ ለመመከት የሚያስችል ቋሚ የቴክኒክ ትብብርና የመረጃ ልውውጥ መንገድ ይከፍታልም ነው ያለው።
አፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ያስፈልጓታል፤ የህዳሴ ግድብም ለዚህ ትልቅ ማሳያ የሆነ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ሲልም ገልጿል።
አፍሪካ በመልክዓ ምድራዊ ወሰኖች ሳትታጠር በኢኮኖሚና በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር ትልም ያለው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና እውን እንዲሆን እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶች ወሳኝ ድርሻ አላቸው።
ግድቡ አፍሪካውያን የራሳቸውን ጉዳዮች በዲፕሎማሲያዊ ብስለትና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት አቅም እንዳላቸው የሚያሳይ ነውም ብሏል።
ጆሽ ዊልሰን በጽሑፉ ላይ እንዳሰፈረው፣ የውሃ ሀብት የግጭት መፍጠሪያ ሳይሆን የጋራ ብልጽግና ማዕከል መሆን አለበት።
የአፍሪካ ኅብረት መርሆዎችን መሰረት በማድረግ፣ የጋራ ሀብቶች ለጋራ ብልጽግና እንዲውሉ ማድረግ የዘመኑ የዲፕሎማሲ እና የልማት ዋና ትኩረት ሊሆን ይገባል ነው ያለው።
ጆሽ ዊልሰን በጽሑፉ ላይ እንዳሰፈረው፣ የውሃ ሀብት የግጭት መፍጠሪያ ሳይሆን የጋራ ብልጽግና ማዕከል መሆን አለበት።
የአፍሪካ ኅብረት መርሆዎችን መሰረት በማድረግ፣ የጋራ ሀብቶች ለጋራ ብልጽግና እንዲውሉ ማድረግ የዘመኑ የዲፕሎማሲ እና የልማት ዋና ትኩረት ሊሆን ይገባል ነው ያለው።
የህዳሴ ግድብ ስያሜ በራሱ የአፍሪካን ትንሳኤ እና የራስ መተማመን መንፈስ የሚያንጸባርቅ መሆኑን አመልክቷል።
ግድቡ ዜጎች በልማት ላይ ያላቸው ቀጥተኛ የባለቤትነት ስሜት በመላው አፍሪካ እንዲስፋፋ እና የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ገበያዎች እንዲጠናከሩ በር ይከፍታል።
ጆሽ ዊልሰን ጽሑፉን ሲያጠቃልል፣ የህዳሴው ግድብ የአፍሪካ ልማትና አንድነት እንዲሁም ሕዝቦችን የሚያስተሳስር ቋሚ ድልድይና ዓርማ ሆኖ ይቀጥላል ሲል ገልጿል።