የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤መስከረም 1/2019 (ኢዜአ)፦ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአውስትራሊያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በአውስትራሊያ ማህበራዊ እና ባህላዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ትልቅ ስፍራ አንስተዋል።
በዓሉ ከደማቅ ባህላዊ ትውፊቶቹ ባሻገር፣ የኢትዮጵያን ጥልቅ ታሪክና ማንነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች ተሰባስበው የቆዩ እሴቶቻቸውን ይበልጥ የሚያጸኑበት፣ እንዲሁም የጋራ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት ልዩ ወቅት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያውያን በአውስትራሊያ መሬት ላይ ሆነው የትውልድ ግንዳቸውን ጠብቀው ማክበራቸው ለአውስትራሊያ ብዝሃነት ትልቅ እሴት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ድርጊት ማህበረሰቡ በአውስትራሊያ ታሪክ ውስጥ እየጻፈው ላለው አዲስ ምዕራፍ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰላም፣ የብልጽግና እና የደስታ እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።