ቀጥታ፡

በጎነት የሰብዓዊ ክብር መሠረት፤ የመደመር መንግሥት የሰው ተኮር ልማት የተስፋ አድማስ

በጎነት ከኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ኑሮና እንቅስቃሴ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ፣ ከራስ ቀንሶ ለሌሎች መድረስ የሚገለጽበት ከፍ ያለ ሰብዓዊ እሴት ነው። 

በጎነት የግለሰብን ችግር ብቻ የሚያቃልል ተግባር አይደለም። የዜጎችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶችን በመሙላት አብሮነትን፣ መተሳሰብንና የጋራ ኃላፊነትን የሚያጠናክር የማህበራዊ ኃላፊነት ውልም ነው።

''ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው ጌጡ፤ ለአንድ ሰው ሸክሙ” እንዲል የሀገር ብሂል ሰዎች በአንድነት ቆመው ለአንድ መልካም ዓላማ ከተባበሩ ለመፍታት የማይቻል ችግር እንደሌለ በተግባር የሚያሳዩ ብዙ አብነቶች አሉ።

በተለይም በሰው ተኮር ልማትና በበጎ ፈቃድ የሚከናወኑ የቤት ግንባታና እድሳት ሥራዎች ችግርን ከመቅረፍ ባለፈ የሰዎችን ሰብዓዊ ክብር የሚመልሱ የተስፋ ምንጭ ተግባራት ሆነዋል።


 

ባለፉት ዓመታት በሀገር አቀፍም ሆነ በአዲስ አበባ በበጋና ክረምት ሰው ተኮር የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች በርካታ ዜጎችን ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና ወደ ልዕልና እንዲሸጋገሩ አስችሏል።

ከእነዚህ የሰው ተኮር ተግባራት ተጠቃሚ ከሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል በመኖሪያ ቤት ችግር ምክንያት ኑሯቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ ነዋሪዎች ይገኙበታል።

ቤት ለአንድ ሰው የመኖሪያ ቦታ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የዜጎችን የደህንነት፣ የክብር፣ የመረጋጋትና ዘላቂ የተስፋ ወጋገን የሚያቆራኝ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። 

ስለዚህ ለአንድ ቤተሰብ የሚገነባ ወይም የሚታደስ ቤት ከግንባታ ዕቃና ከግድግዳ በላይ ትርጉም አለው፤ የተሰበረ ተስፋን ይጠግናል፣ የተረሳ ክብርን ይመልሳል፣ ለነገም አዲስ እድል ይከፍታል።

በአዲስ አበባ በበጎ ፈቃደኞች፣ በባለሀብቶችና በመንግሥት የጋራ ጥረት ቤት ተገንብቶላቸው እፎይታን ያገኙ ነፍሶችም በርካቶች ናቸው።


 

ወይዘሮ መስከረም ሰለሞን እንደሚሉት፤ ከዓመታት በፊት ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ፒያሳ አካባቢ ለሰው ልጅ ክብርን በማይመጥን ጎስቋላ ቤት ውስጥ ሕይወትን ይመሩ ነበር።

በተለይም ክረምት በመጣ ቁጥር የጎርፍና የዝናብ ፍሳሽ አደጋ በከፍተኛ ጭንቀት እንዲያሳልፉ ያስገድዳቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

በሳር ቤት አካባቢ በተሰራላቸው ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር የተሰጣቸው የመኖሪያ ቤት አዲስ የሕይወት ተስፋን እንዳጎናጸፋቸው አስረድተዋል።

ይህንም ለመኖር ከማይመች ቦታ ወጥቼ ወደ አማረ ቤት በመግባቴ እንደገና የመወለድ ያህል ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ወይዘሮ መስከረም ታሪክ ሁሉ የሌሎች ነዋሪዎች የቤት ግንባታና ዕድሳት ሥራዎች ተሞክሮ የሚያሳየው የቁሳዊ እፎይታ ብቻ ሳይሆኑ ሰብዓዊ ክብርን የሚያጎናጽፉ የተስፋ ውጤቶች መሆናቸውን ነው።


 

በአንድ ወቅት ከፎቅ ላይ ባጋጠማት የመውደቅ አደጋ ሳቢያ የአካል ጉዳት ያጋጠማት ታሪክ ሙሉጌታ፤ በአዲስ አበባ በኪራይና በመንግሥት ቤት ከቤተሰቧ ጋር ሕይወትን ስትገፋ እንደነበር ገልጻለች።

የአካል ጉዳተኛ ከሆነች በኋላ ቀደም ሲል ትኖርበት የነበረው ቤትና አካባቢ ከቦታ ቦታ እንደልብ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንደነበር በማስታወስ፤ ከቤተሰቧ ጋር ይኖሩበት ከነበረው ባምቢስ አካባቢ ወደ ሳር ቤት አካባቢ የመኖሪያ ቤት ማግኘቷ በሕይወት ዘመን ያገኘሁት ትልቅ የተስፋ ስጦታዬ ነው ብላለች።

ቤቱ እንደልብ መንቀሳቀስ የሚያስችል፣ መሠረታዊ የመኖሪያነት መስፈርቶች የተሟላላት መሆኑ ሕይወቴን በትልቅ እፎይታ እንድመራ አስችሎኛል ስትል ተናግራለች።

በሰው ተኮር ፕሮጀክት የሚገነቡ ቤቶች የሚያመጡት ለውጥ ለአካል ጉዳተኞች ብቻ የሚወሰን አይደለም። በቤት ውስጥ ልጆች፣ አረጋውያን፣ የሀገር ባለውለታዎችና መላ ቤተሰብ እንዲሁም የተሻለ ኑሮን ለመፍጠር የሚታገሉ እናቶችና አባቶችም የዚህ ተግባር ተጠቃሚዎች ናቸው። 

በዚህም በጎነት የአንድን ሰው ዛሬ ከማሻሻል ባለፈ የአንድ ቤተሰብን ነገ የሚቀርጽ ኃይል መሆኑን ያሳያል።


 

ወይዘሮ ጽጌሬዳ ጎበና ፤ ለረጅም ዓመታት ፒያሳ አካባቢ ለመኖር ምቹ ባልሆነ ቤትና ሰፈር ከአንድ ልጃቸው ጋር ይኖሩ ነበር። 

በፒያሳ አካባቢ የሕይወት ቆይታ ዘመናቸውም ልዩ ድጋፍ የምትሻው ልጃቸው እንደልቧ መንቀሳቀስ የማትችልበትን በርካታ የሰቆቃ ጊዜያት እንዳሳለፈች አስታውሰዋል።

በዚህ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እያሉ በሳር ቤት አካባቢ አዲስ ቤት ማግኘታቸው እንደገና የመወለድ ያህል ትልቅ እፎይታን እንደቸራቸው ገልጸዋል።

የተሰጣቸው ቤት ለልጃቸው እንቅስቃሴ ምቹ ከመሆኑ ባለፈ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን እንዲከተሉ ያስቻለ ታላቅ የሕይወት ብስራት መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ ታሪኮች የሚያስረዱት አንድ ቤት ሲታደስ ግድግዳና ጣሪያ ብቻ አለመሆኑን ነው። ከቤቱ ጋር የነዋሪው ተስፋ፣ የቤተሰቡ መረጋጋትና የሰው ልጅ ክብርም አብሮ ይታደሳል። 

በዚህም በጎነት የችግር መፍቻ ብቻ ሳይሆን ከጊዜ ጊዜ የተስፋ ማስፈንጠሪያና ሰብዓዊ ክብር ማጎናጸፊያ ተግባር እየሆነ መጥቷል።


 

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቤታቸው ከታደሰላቸው መካከል ታየሁ መኮንን እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል ይኖሩበት የነበረው ቤት 'ቤት ነው ለማለት እንኳን አያስደፍርም' ነበር።

ዛሬ ግን ታሪካቸው ተቀይሯል። በበጎ ፈቃደኞች አማካኝነት የመኖሪያ ቤት ችግራቸው ተቀርፎ፣ 'ቤቴ በመታደሱ ያለ ሀሳብ ጎኔን ማሳረፍ ችያለሁ' ሲሉም ወይዘሮ ታየሁ ገልጸዋል።

ይህ አንድ ነዋሪ ያገኘው የቤት ለውጥ ብቻ አይደለም። ከዓመታት የጭንቀት ኑሮ ወደ መረጋጋት የተሸጋገረ ሕይወት ነው። ከስጋት ወደ እፎይታ፣ ከተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፋ የተደረገ ጉዞ ነው።

ለበርካታ ዓመታት በማይመች ቤት ኑሮ ሲገፉ እንደቆዩ የገለጹት ወይዘሮ ዘውዲቱ ገብረማርያም ደግሞ፤ አሁን ላይ ቤታቸው በመታደሱ ደስ ብሏቸው የሚኖሩበትን ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።


 

በሰው ተኮር የልማት መርሃ ግብር አቅመ ደካማ ወገኖችን ለመደገፍ የሚከናወኑ ተግባራትም የበርካቶችን ተስፋ የሚያለመልም አስደናቂ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

እነዚህ የነዋሪዎች ምስክርነቶች በጎነት በተግባር ሲገለጽ የሰውን ክብር እንደሚያጎናጽፍ፣ የተሰበረ ተስፋን እንደሚያድስና ለነገ የሚያስብ ሕይወትን እንደሚፈጥር ያረጋግጣሉ። 

በተለይም እናቶች፣ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞችና የሀገር ባለውለታዎች የሚያገኙት ድጋፍ በቁሳዊ እርዳታ ብቻ የሚመዘን ሳይሆን  'እናንተም የዚህ ሀገር ክብር ናችሁ' የሚልን ሰብዓዊ መልዕክትን ያስተላልፋል።

በዚህ ረገድ የመደመር መንግሥት ሰው ተኮር ልማትን እንደ የልማት ፖሊሲ አቅጣጫ በመያዝ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍተቶች በመሙላት ተስፋን የሚያለመልሙ ተግባራትን እያጠናከረ ይገኛል።

የቤት ግንባታና ዕድሳት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችና ሌሎች ሰው ተኮር መርሃ ግብሮችም ይህንኑ አቅጣጫ በተግባር ከሚያሳዩ ተጨባጭ ለውጦች መካከል ይጠቀሳሉ።

አስተያየት ሰጪዎቹ ዛሬ ላይ ውብና ጽዱ በሆነ ቤት የሚኖሩበት ዕድል የተፈጠረው መንግሥት፣ ባለሀብቶችና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች ባከናወኑት መልካም ተግባር በመሆኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በአዲስ አበባ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት አረጋውያንን፣ አቅመ ደካሞችና የሀገር ባለውለታዎችን አመቺ መጠለያ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በእርግጥም የበጎነት ዋጋው በሚሰጠው የቁሳቁስ መጠን ብቻ አይለካም። በሰው ልብ ውስጥ በሚፈጥረው ተስፋና በሕይወት ላይ በሚያመጣው ለውጥ ይመዘናል። 

የተሰራው ቤት ለአንዲት እናት የእፎይታ ምንጭ፣ ለአንድ አረጋዊ የክብር መገኛ፣ ለአካል ጉዳተኛ ደግሞ በራስ መተማመንና ነፃነት መገለጫ ይሆናሉ።


 

ይህም ሰው ተኮር ልማት ማለት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት ብቻ ሳይሆን፣ የአንድ ዜጋን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ የአንድ ቤተሰብን ተስፋ ማደስና የአንድን ሰው ክብር ማስመለስ ጭምር መሆኑን ያሳያል።

በጎነት ከአንድ ሰው ወደ ሌላው የሚሸጋገር ቀላል የመልካም ተግባር መገለጫ ቢመስልም በጋራ ሲተገበር ማኅበረሰብን የመለወጥ ታላቅ ኃይል አለው።

የእነዚህ ነዋሪዎች ታሪክም ይህንኑ ያረጋግጣል። ከተስፋ መቁረጥ ወደ ተስፋ፣ ከስጋት ወደ እፎይታ፣ ከአስቸጋሪ ኑሮ ወደ የተሻለ ኑሮ የተሸጋገሩ ሕይወቶችን ያሳያል።

ስለሆነም በጎነትን እንደ የአንድ ጊዜ ዘመቻ ሳይሆን እንደ የማኅበረሰብ የጋራ እሴት ማጠናከር፣ ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን መደገፍና ሰው ተኮር ልማትን ማስቀጠል የጋራ ኃላፊነት ነው። 

ዛሬ የተሰራ ቤት ከግድግዳ በላይ ነው። የነገ ተስፋ መሰረት ነው። ዛሬ የተዘረጋ የበጎነት እጅም ከአንድ ሰው የሚተርፍ ለብዙዎች የሚደርስ የሰብዓዊነት ብርሃን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም