ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት ለሀገራችን ዕድገት በትጋት እንሰራለን

ደሴ ፤ መስከረም 1/2019 (ኢዜአ)፦ አዲሱ ዓመት አንድነታችንን ጠብቀን ሰላምና ልማታችንን በተሻለ መልኩ ለማረጋገጥ  በትጋት የምንሰራበት ዓመት ነው ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የሀርቡ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች ገለፁ።

የከተማዋ ነዋሪዎች በአዲሱ ዓመት ለሀገርና ለከተማቸው ሰላምና ልማት በቁርጠኝነት  ለመስራት ማቀዳቸውን ነው የተናገሩት።

የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ዚነት ሁሴን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በአዲሱ ዓመት የከተማዋን ሰላምና እድገት ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ውስጥ በመሳተፍ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።

አዲሱ ዓመት የተሻለች ኢትዮጵያን የምናይበት ዓመት ይሆናል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። 

የአካባቢያቸውን ጸጥታ በጋራ ከመጠበቅ ጎን ለጎን በትምህርት፣ በጤና እና በመሰረተ ልማቶች ግንባታ ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።


 

ሌላው የሀርቡ ከተማ ነዋሪ አቶ ሁሴን የሱፍ በበኩላቸው፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የመከባበርና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በዓሉን በፍቅርና በደስታ እያከበሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በአዲሱ ዓመት አንድነታችንን ጠብቀን ለከተማችን ሰላም፣ ልማትና ሁለተናዊ ብልጽግና በትጋት የምንሰራበት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት። 

በአዲሱ ዓመት ጥሩ ተስፋ ሰንቀን አንድነታችንንና የአካባቢያችንን ሰላም  የምናስቀጥልበት ነው ያሉት ደግሞ አቶ መሀመድ እንድሪስ ናቸው።

 

ከባለፈው ዓመት ድክመቶቻችን ተምረን ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና የድርሻችንን ለመወጣት ከወዲሁ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የከተማዋን ዘላቂ ሰላም ለማስጠበቅ እና የልማት ስራዎችን ለማፋጠንም ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም