ቀጥታ፡

አዲስ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀበት- አዲስ ዓመት

መስከረም 1/2019 (ኢዜአ)፦ አዲስ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀበት አዲስ ዓመት

የኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት (መስከረም 1) የዓመት መለወጫ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ መታደስ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የይቅርታ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ታላቅ ህዝባዊ በዓል ነው። በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መሠረት አዲሱ ዓመት የሚጀምረው የክረምቱ ድቅድቅ ጨለማና ዝናብ አልፎ፣ ሰማዩ ጠርቶ፣ ምድሩ በብርሃንና በአደይ አበባ በሚሸፈንበት በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ነው።

«እንቁጣጣሽ» የሚለው ስያሜ «እንቁ ዕጣ ለአንቺ» ወይንም “እንኳን ደህና መጣሽ” በማለት በከበሩ ዕንቁዎች የተደረገ አቀባበል ጋር ተያይዞ የተሰየመ ስለመሆኑም ይነገራል።

በአዲስ ዓመት ክረምቱ አልፎ መስከረም ሲጠባ አበቦች ያብባሉ፣ ጥርት ያሉ ወንዞች ይታያሉ፤ ምድር በአረንጓዴ ውበት ታሸበርቃለች። የተፈጥሮ ማሸብረቅን ተከትሎም የሰዎችም ህይወትና ተስፋ አዲስ የሚሆንበት ምልክት መሆኑ ይነሳል።

በአሮጌው ዓመት የነበሩ ቅሬታዎች፣ ጥላቻዎችና አለመግባባቶች ተወግደው አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትበት፣ ዘመድ ከዘመድ የሚጠያየቅበትና ይቅር የሚባባልበት ወርቃማ ጊዜም መሆኑ ይነገራል።

በአዲስ ዓመት መባቻ በየቤት ደጃፍና በየመንደሩ «ችቦ» ይበራል፤ የችቦው መበራት ጨለማውን አሮጌ ዓመት ሽኝተን፣ በብርሃን የተሞላውን አዲስ ዓመት መቀበላችንን የሚያመላክትም ነው። «እዮሃ መስከረም ጠባ...» እየተባለም ይዜምለታል።

በበዓሉ ዕለት ጠዋት ልጃገረዶች ባህላዊ አልባሳታቸውን ለብሰው፣ ከበሮ በመምታት «አበባዮሽ» እያሉ በየቤቱ በመዘዋወር የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞት በማቅረብ በስጦታና ሙገሳ እንዲሁም በምርቃት የሚሸኙበት ነው።

ወንዶች ልጆች ደግሞ በአደይ አበባና በተፈጥሮ ምስሎች ያሸበረቁ ስዕሎችን በወረቀት ላይ በመሳል «እንኳን አደረሳችሁ» በማለት ለጎረቤትና ለዘመድ አዝማድ ያበረክታሉ።

በእለቱ የሀገር ባህል ምግብ ተዘጋጅቶ ቤተሰብ፣ ዘመድና ጎረቤት በአንድ ላይ ይሰበሰባል፤ የቡና ስነ-ስርዓት ተካሂዶ በእንቁጣጣሽ የተቆረጠው አደይ አበባና ሳር ይጎዘጎዛል በዚህ መልኩም ክብረ በዓሉ ይቀጥላል።

በዚሁ መሰረትም የዘንድሮውን አዲስ ዓመት ኢትዮጵያዊያን በታላቅ ደስታና ተስፋ ተቀብለው በማክበር ላይ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ማንሰራራት በብዙ መልኩ የተገለጠበትና ዘለቄታዊ መሰረቶች የተጣሉበት 2018 ዓ.ም ተጠናቆ ወደ 2019 ዓ.ም ስንሸጋገር ያለፉትን ስኬቶች በማጠናከርና ጉድለቶችን ለመሙላት በመዘጋጀት ነው።

እንደ ሀገር እየተከናወኑ ያሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን በማስቀጠልና የተጀመሩትን ታላላቅ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው እቅድ መሰረት ለስኬት ለማብቃት በመትጋት መሆንም ይኖርበታል።

አዲስ የተስፋ ብርሃን በፈነጠቀበት አዲስ ዓመት አዲስ አስተሳሰብ በመሰነቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዘላቂ ሰላምና ለልማት በመነሳት መሆን ይኖርበታል።

በአዲስ ዓመት የመስከረም ብርሃን ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የፍቅር፣ የብልፅግና እና የከፍታ ዘመን ይዞ እንዲመጣ እንመኛለን! መልካም አዲስ ዓመት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም