ቀጥታ፡

የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2019 (ኢዜአ)፦ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች እና አምባሳደሮች ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

መጪው አዲስ ዓመት ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የአንድነት እና የብልጽግና እንዲሆን እንዲሁም  ከየሀገራቱ ጋር ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አምባሳደር አብደላ አል ሸምሲ ባስተላለፉት መልዕክት ለአዲሱ ዓመት እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ስትራቴጂካዊ አጋርነት እና ወዳጅነት በጋራ ፍላጎትና መከባበር ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል።

አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር እና የልማት እንዲሆን ተመኝተዋል።




በኢትዮጵያ የማሌዥያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሞህድ አፈንዲ አቡበከር በበኩላቸው፣ ለኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት አደረሳችሁ ብለዋል።

አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የብልፅግና፣ የጤና እና የደስታ እንዲሁም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።




በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር ኒርማላ ኢንዱማቲ ዲያስ ፓራናቪታና በበኩላቸው፣ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትና ብልፅግናን እንዲሁም ለተቋማቷ ጥንካሬን ይዞ እንዲመጣ ተመኝተዋል።

በስሪላንካ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ወዳጅነት እና የባህል ትስስር ይበልጥ እያደገ እንደሚሄድ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።




በኢትዮጵያ የጀርመን ተጠባባቂ አምባሳደር ፈርዲናንድ ቮን ዌይሄ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የሰላም፣ የአንድነት እና ብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።

በፊንላንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ፒርጆ-ሊሳ ሄይኪላ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን የደስታ እና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።




አዲሱ ዓመት በፊንላንድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ወዳጅነትና ትብብር እንደሚጎለብት ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሚርጃ ክሮኔ በአዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የጸና አጋርነት የሚጠናከርበት እንዲሆን ተመኝተዋል።




የሁለቱ ሀገራት ቀጣይ ጉዞ በብልጽግና፣ በሰላም እና በዘላቂ ልማት የተሞላ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አብርሃም ንጉሴ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና እስራኤል የረጅም ዓመት ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ገልጸው ይህንን የረጅም ዘመን ወዳጅነታችንን አጠናክረን በመቀጠል ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል።




መላው ኢትዮጵያውያንን እንኳን ለአዲሱ ዓመት 2019 ዓ.ም በሰላም አደረሳችሁ፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣የእድገትና የፍቅር ዘመን እንዲሆንላችሁም ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት በአዲሱ ዓመት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር ናቸው።




አምባሳደርዋ በኢትዮጵያ እና በአውሮፓ ህብረት መካከል እያደገ የመጣው አጋርነት ተስፋ ሰጪ መሆኑን በመግለጽ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኤምስበርገር አገሪቷ ወደ 2019 ዓ.ም ስትሸጋገር ለኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ብልፅግና፣ መልካም ጤንነትና ደስታን ተመኝተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቢሮ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የደስታና እና ብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢራን፣ ፓኪስታን፣ ሜክሲኮ፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ ኤምባሲዎችም የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም