የአዲስ ዓመት በዓልን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በማሳለፋችንና በተበረከተልን ስጦታ ደስታ ተሰምቶናል - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ ዓመት በዓልን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በማሳለፋችንና በተበረከተልን ስጦታ ደስታ ተሰምቶናል
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 1/2019 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ ዓመት በዓልን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር በማሳለፋችንና በተበረከተልን ስጦታ ልዩ ደስታ ተሰምቶናል ሲሉ ስጦታው የተበረከተላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አዲስ ዓመትን በማስመልከት ማዕድ አጋርተዋል።
ይህ መልካም እሴት በሰርክ እና እንዲህ ባለ የበዓላት ወቅት በሰፊው ባህል ሆኖ መቀጠሉ ከትላንት እስከ ዛሬ የኢትዮጵያውያን መገለጫ መሆኑን ማሳያ ነው።
ከዓመት ወደ ዓመት መሸጋገር፣ ዓመቱንም በመተሳሰብ መጀመር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዓላትን በበጎነት ተግባር የመቀበል ልምምድ ከሆነም ሰነባብቷል።
ዘንድሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ለአቅመ ደካማ ወገኖች አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ በማጋራት የበዓል ስጦታም አበርክተዋል።
በበዓል ያለውን ተካፍሎ በመተሳሰብ ማሳለፍ ከሚጋራው ማዕድም በላይ የኢትዮጵያውያንን የመተሳሰብና የአብሮነት መንፈስ የሚያጎናጽፍ፣ የመልካም ምኞት መገለጫ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ የ2019 ዓ.ም የአዲስ ዓመት ብሥራትን ተከትሎ ባዘጋጁት የማዕድ መጋራት መርሃ ግብር የተካፈሉ ወገኖችም ዓመቱን በታላቅ ምስጋና ጀምረዋል።
ወይዘሮ በቀለች ሙለታ እንደሚሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ድሆችን፣ አቅመ ደካሞችን፣ ሴቶችንና እናቶችን አክባሪ፣ ደግ፣ ሩህሩህ፣ ድንቅና ጀግና መሪ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ቀዳማዊት እመቤት ማዕድ በማጋራት፣ የበዓል ስጦታንም ስላበረከቱላቸው ታላቅ ምስጋና በማቅረብ በዓሉን በደስታ እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል።
አቶ ጸጋዬ ገብረማርያም በበኩላቸው፤ ለተበረከተላቸው ማዕድና የበዓል ስጦታ ምስጋና በማቅረብ፣ መጪው አዲስ ዓመት የኢትዮጵያ ዕድገትና ከፍታ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል።
መረዳዳትና መተሳሰብ አዲሱን ዓመት በብሩህ ተስፋ ለመቀበል የሚጋብዝ በፈጣሪም የተወደደ በጎ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ አቶ አሕመድ አልበደዌ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ባለቤታቸው አቅመ ደካሞችን ቤተ መንግሥት ድረስ በመጥራት ላበረከቱላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ለተበረከተላቸው ስጦታም የአዲስ ዓመት በዓልን በብሩህ ተስፋ በመቀበል የኢትዮጵያን ብሩህና የመተሳሰብ ዘመን የሚያበስር መሆኑን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ፈይሴ ሙሉ በበኩላቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩና ባለቤታቸው የተበረከተልኝ ስጦታ በዓልን ከቤተሰቤ ጋር በታላቅ ደስታ በማሳለፍ መጪውን ዘመን በብሩህ ተስፋ መቀበል የሚያስችለኝ ነው ብለዋል።
ሌላው ድጋፍ የተደረገለት ተፈሪ ሾንጋ በበኩሉ እንደሚገልጸው፤ አሁን የተበረከተላቸው ድጋፍ በዓሉን በደስታ ማሳለፍ የሚያስችላቸው ነው።
አዲሱ የኢትዮጵያ ዓመት የብሩህ ተስፋ ማብሰሪያ መሆኑን በመግለጽ ለተበረከተላቸው ስጦታ ምስጋና ያቀረቡት ደግሞ ወይዘሮ ጌጡ ዋቄ ናቸው።
ደስያ አሕመድ በበኩሏ፤ ለተበረከተላት የበዓል ስጦታና ማዕድ ማጋራት ምስጋና አቅርባለች።