ቀጥታ፡

አዲሱ አመት የመከላከያ ሠራዊታችን አቅም ይበልጥ የሚጠናከርበት ዓመት ይሆናል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ፤ጳጉሜን 5 /2018 (ኢዜአ)፦አዲሱ ዓመት የመከላከያ ሠራዊታችን አቅም ይበልጥ የሚጠናከርበትና ዝግጁነቱ የሚያድግበት ዓመት ይሆናል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ለመከላከያ ሠራዊት አባላት ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ 2018 በርካታ ፈተናዎች የተጋፈጥንበት ዓመት ቢሆንም፣ የመከላከያ ሠራዊቱ የተቀመጡ ሀገራዊ ግቦችንና ዕቅዶችን በተቀናጀ አሠራር በማሳካት የተሰጠውን ኃላፊነት በከፍተኛ ብቃት የተወጣበት ዓመት ነበር ብለዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት የሠራዊቱ ዋና ትኩረት የሀገርን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ፣ ህዝብን መጠበቅና የልማት ጉዞዎችን ከዕንቅፋት መከላከል እንደነበር ጠቁመው፤ በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች መረጋጋት በመፍጠር ህዝቡ ወደ መደበኛ ኑሮው እንዲመለስ መደረጉን አስረድተዋል።

አክለውም ዘላቂ ሰላም በወታደራዊ አቅም ብቻ የማይረጋገጥ በመሆኑ ህዝቡ ለሰላም የሚያበረክተውን ሚና ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል 2018 ዓ.ም የመከላከያ አቅምን ከዘመኑ ጋር ለማዛመድ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል አሠራር የመሸጋገር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመታጠቅ፣ የምድርና የአየር ኃይል አቅምን የማሳደግ እንዲሁም የመከላከያ ኢንዱስትሪን በሀገር ውስጥ ምርቶች የማጠናከር ሰፊ ሥራ የተሠራበት ዓመት መሆኑን ገልፀዋል።

በመጪው 2019 ዓ.ም የመከላከያ ሠራዊቱ ሁለት ዋና ዋና ትኩረቶች ይኖሩታል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የመጀመሪያው የሀገርን ሰላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሠራዊቱን የማድረግ አቅም፣ የሰው ኃይል፣ የሥልጠና፣ የመሠረተ ልማት እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ልማት ሥራዎችን ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሆነ አስታውቀዋል። 

አዲሱ ዓመት የመከላከያ ሠራዊታችን አቅም ይበልጥ የሚጠናከርበትና ዝግጁነቱ የሚያድግበት ዓመት ይሆናል ሲሉም አክለዋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች፣ መኮንኖች፣ ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን ተመኝተው፤ አዲሱ ዘመን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ለህዝባችን ደህንነትና ብልፅግና፣ ለሰራዊታችን የበለጠ አቅም፣ ዝግጁነትና ስኬት የሚያመጣ ዓመት ይሁንልን ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም