ቀጥታ፡

አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ለውጥ ወደ ሌላ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ለውጥ ወደ ሌላ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት ድልድይ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 2019 ዓ.ም አዲስ ዓመትን በማስመልከት ልዩ የአዲስ ዓመት ዋዜማ የሙዚቃ ድግስ አዘጋጅቷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተለያዩ ሀገራት
አምባሳደሮችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ፣ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ታድመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የተጠናቀቀው የ2018 ዓመት በብዙ ስኬቶች ታጅቦ የተሻገረ ነው።

ለኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ለውጥ ወደ ሌላ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የምንሸጋገርበት ድልድይ ነው ብለዋል።

አዲሱ ዓመት ባለፉት ዓመታት የገጠሙንን ፈተናዎች ወደ ዕድልና ድልድይ የምንቀይርበት፤ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ መሰረት የምንጥልበት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

ትጋት፣ ትብብር፣ ቅንጅት እና ብርታት ወደ ብልጽግና የምንሸጋገርባቸው መንገዶች መሆናቸውን ገልጸው፤ ለኢትዮጵያውያን ካለፈው የወደፊቱ ያጓጓል ብለዋል።

ዘመን ጥሎ ሂያጅ መሆኑን በማንሳት፤ ትልቁ ቁም ነገር በተሰጠን ዘመን ምን አዲስ ነገር ሠራን የሚለው ሊያሳስበን ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ አበባ ጊዜዋን አላባከነችም፤ ይልቁንም የተጉሳቆሉ ጎኖቿን እያደሰች የምትሄድ ውብ ከተማ ሆናለች ብለዋል።

አዲስ አበባ 365 ቀናት 24/7 በመስራት ጠንካራ የሥራ ባህል እየገነባች ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ባስመዘገበችው የለውጥ እምርታ የዓለም አቀፍ መስህብና ዜና መሆኗን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ በሰው ተኮር ሥራዎቿ ለነዋሪዎቿ ቅድሚያ የምትሰጥ፣ እንባ አባሽ፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የምታረጋግጥ፤ ዘላቂ ልማትን የምታሳልጥ ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።

በቀጣይ ጊዜያችንን ለከፋፋይ ትርክቶች ቦታ ሳንሰጥ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን በማጎልበት የጸናችና የታፈረች ኢትዮጵያን መገንባታችንን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።

ጊዜያችንን ለቁም ነገር በመጠቀም እውቀታችንና ክንዳችንን ለሀገርና ትውልድ ግንባታ ለማዋል መትጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም