ቀጥታ፡

የሀዋሳ ከተማ የተቸረችውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀም በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል

ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ የሀዋሳ ከተማ የተቸረችውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀምና ለህዝብ ጥቅም ለማዋል በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ፡፡

የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ግንባታ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋናና የዕውቅና መርሀ ግብር እየተካሔደ ነው።


 

''ሀዋሳ ታመሰግናችኋለች'' በሚል መሪ ቃል የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በተገኙበት ነው መርሃ ግብሩ እየተካሔደ የሚገኘው።

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እንደገለጹት በ2018 በጀት ዓመት የታቀዱ ተግባራት በቅንጅት ተከናውነው ውጤት ያስገኙበት ነው።

ከተማዋ የተቸረችውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አልምቶ ለመጠቀምና ለህዝብ ጥቅም ለማዋል የተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል።

ከእነዚህም አንዱ የሐይቅ ዳር ልማት ፕሮጀክት መሆኑን አንስተው በመንግስትና በአጋር አካላት ተሳትፎ ግንባታው እየተፋጠነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።


 

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን ገጽታና ውበት እንዲሁም ተወዳዳሪነትና ተመራጭነትን በማሳደግ ረገድ ትርጉም ያለው ውጤት እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በዚህ የልማት ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙ አካላትን ያመሰገኑት ከንቲባው የዛሬው የምስጋናና ዕውቅና መርሀ ግብር የተዘጋጀው ተሳትፎውን የበለጠ ለማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላት፣ባለሀብቶች፣የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም