የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ):- የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
አፈ ጉባኤው በመልዕክታቸው፤ የተፈጥሮ ዑደት የሆነው የዘመን መለወጥ ሰዎች ከትናንት እንዲማሩ እና ነገን በተስፋ ለመገንባት አዲስ ጉዞ እንዲጀምሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በብዝኀ ቋንቋዎች፣ ማንነቶች እና እሴቶች ያሸበረቀች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህ ብዝኃነት የጋራ ውበት እና ሀብት እንጂ የመለያያ ግንብ እንዳልሆነ አንስተዋል።
መጪው ዓመት የልዩነት ትርክት የሚደርቅበት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጸናበት እና በአዲስ ወኔ ወደ ልዕልና የሚሸጋገሩበት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በላቀ ደረጃ ለመወጣት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
ምክር ቤቱ በሕዝቦች እኩልነት ላይ የተመሠረተ ኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎች እንዲሰጡ እና የፌዴራልና ክልሎች የገቢ ክፍፍል ቀመር እንዲሻሻል ሰፊ ሥራዎችን አከናውኗል።
አፈ ጉባኤው አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የብልጽግና ዘመን እንዲሆንም ተመኝተዋል።