ቀጥታ፡

የመንግስታዊ አገልግሎቶችን በማዘመን የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል 

ድሬዳዋ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ የመንግስታዊ አገልግሎቶችን በማዘመን የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ገለጹ።

ጳጉሜን  5 "የነገ ቀን" በሚል ስያሜ በድሬዳዋ አስተዳደር በፈጠራና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተመዘገቡ እምርታዎችን የሚያመላክት የፓናል ውይይትና በአውደ ርዕይ ተካሂዷል።


 

ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፣ የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ የነገዋን ታላቅ አገር የመገንባቱ ጉዞ በተጨባጭ ውጤቶች እውን እየሆነ ነው።

የተሻለች እና የበለፀገች አገር ለትውልድ ለማስረከብ በየደረጃው የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ከንቲባው ተናግረዋል።

በተለይ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትን የጨበጠ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ በመገንባት ፈጣንና ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የነዋሪውን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እየተመለሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት በከተማ አስተዳደሩ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጡባቸው ባሉ አከባቢዎች አዎንታዊ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።

በአስተዳደሩ ዲጂታል የአሰራር ሥርዓትን በላቀ ደረጃ ለማሳደግ በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች፣ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና በግል ተቋማት የተጀመሩ የፈጠራና የቴክኖሎጂ የምርምር ሥራዎች የነገዋን ታላቅ አገር ለመገንባት መደላድል እየፈጠሩ ይገኛሉ ብለዋል።


 

በድሬዳዋ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ከሙስና የፀዳ አገልግሎት በመስጠት የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።

የነገ ቀን በድሬዳዋ ሲከበር ከመድረክ በተጨማሪ በአረጋዊያን መጦሪያ ማዕከል ለሚገኙ አቅመ ደካሞች ከንቲባው ማዕድ ያጋሩ ሲሆን የድሬዳዋ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርም ተጎብኝቷል።


 

በስነስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ አብዲ ሙክታር፣ በብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ፣  የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም