አዲሱ ዓመት ያለፉትን ዓመታት ተግባራት የምናጸናበትና የምናሰፋበት፤ አዳዲሶቹን የምንወጥንበት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ ዓመት ያለፉትን ዓመታት ተግባራት የምናጸናበትና የምናሰፋበት፤ አዳዲሶቹን የምንወጥንበት ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለአዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ባሳለፍነው ዓመት ሀገራዊ ምክክሩን ማሳካታችን ቀጣዩ ዓመት በሁሉም ረገድ የተሻለ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ታላላቅ ተግባራትን የከወነችበት 2018 ተሰናበተ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክክሩንም ውጤት ከወዲሁ ማጣጣም ጀምረናል ሲሉም ገልጸዋል።
አዲሱ 2019 ዓመት ያለፉትን ዓመታት ተግባራት የምናጸናበትና የምናሰፋበት ፤ አዳዲሶቹን ደግሞ የምንወጥንበት ነው ብለዋል።
ቀጣዩ 2019 የፖለቲካው ምኅዳር የበለጠ ይሰፋል ያሉት አቶ ተመስገን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተሻለ ፍሬ ያፈራል ሲሉም ገልጸዋል።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በዲጂታል ዘርፎች ያመጣናቸው ውጤቶች የኢትዮጵያን መሪነት ያጠናክሩታልም ብለዋል።
የባሕር በር ለማግኘት የጀመርነው ጥረት ፍሬ ማፍራት ይጀመራል ሲሉ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙዎች አማጽያን በሰላምም በሌላም መንገድ ወደቀናው ጎዳና ይመጣሉ ፤ በ2019 የኢትዮጵያ ታሪክ የበለጠ ማርሹን ይቀይራል ብለዋል።
መንግሥት፣ ሕዝብና የፖለቲካ ኃይሎች በብሔራዊ ጥቅማችን ላይ አንድነት ፈጥረን የኢትዮጵያን እመርታ እውን እናድርግ ሲሉ ጥሪያቸውን የቀረቡት አቶ ተመስገን 2019 የሰላም ፣ የብልጽግና እና የእመርታ ይሁንልን ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።