በዓልን አቅም ለሌላቸው ወገኖች ማዕድ በማጋራት በአብሮነት የማክበር እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በዓልን አቅም ለሌላቸው ወገኖች ማዕድ በማጋራት በአብሮነት የማክበር እሴት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦በበዓል ወቅት አቅም ለሌላቸው ወገኖች ማዕድ በማጋራት በአብሮነት የማክበር እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ።
ከንቲባው የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካማ ወገኖችና ለልማት ተነሺዎች ማዕድ አጋርተዋል።
ከንቲባ ጥራቱ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በአነስተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ህብረተሰቡንና የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የከተማ አስተዳደሩ የልማት ሥራዎች ከማከናወን ጎን ለጎን የህብረተሰቡን ማህበራዊ መስተጋብር የሚያጠናክሩ ተግባራትን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
በዛሬው እለት አቅመ ደካሞች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ በግ እና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ምርቶችን በማጋራት አብሮነቱን መግለጹን ጠቁመዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ዜጎች መካከል አቶ ባልጉዳ ጳውሎስ፣ አቶ በቀለ በንቲ እና ወይዘሮ ማስረሻ ሔርዳሮ በበኩላቸው፤ የተደረገላቸው ድጋፍ የዘመን መለወጫ በዓሉን በደስታ ለማሳለፍ ስለሚያስችላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል ።
በከተማዋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ከ1ሺህ 500 ለሚበልጡ ዜጎች ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት ወልደጻዲቅ ናቸው።