ዲጂታል ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ አገልግሎት አሰጣጥና የሥራ ዕድል እያሰፋ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ አገልግሎት አሰጣጥና የሥራ ዕድል እያሰፋ ነው
ጅግጅጋ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ) ፦ዲጂታል ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ አገልግሎት አሰጣጥን እያቀላጠፈና የሥራ እድልን እያሰፋ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን ገለጹ።
የጳጉሜን 5 "የነገ ቀን" በሚል ስያሜ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከበረ ሲሆን በሶማሌ ክልል ደረጃም ቀኑ በጂግጂጋ ከተማ በተለያዩ ዲጂታል የንቅናቄ መርሃ-ግብሮች ተከብሯል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም እንደገለጹት፤ በክልሉ በቴክኖሎጂና በሰው ኃይል ልማት ላይ በስፋት በመስራት ሁለንተናዊ እድገትን በዘላቂነት ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው።
በተለይ ዲጂታል አገልግሎትን በማስፋፋት ለአገልግሎት አሠጣጥ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለክልሉ የኢኮኖሚ አቅም መጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ አበረታች ውጤቶች ተገኝቷል ብለዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያን ማረጋገጥ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም ዘርፎች አሰራርን በማዘመን ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም አስረድተዋል።
ለዚህም ስኬት የተቋማት የማስፈጸም አቅምን መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በክልሉ ተቋማትን በቴክኖሎጂ አቅርቦትና በሰው ኃይል የማደራጀት ሥራው ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል።
ለአብነትም በክልሉ የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍ 13 መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎች መገንባታቸውን ጠቁመዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት መንግሥት ለዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ የሠጠው ልዩ ትኩረት የነገን የሀገሪቱን አድገት ለማፋጠን የሚያግዝ ነው።
በዲጂታል ዘርፍ የኢትዮ ኮደርስ፣ የስታርትአፕ እና የዲጂታል ክህሎት ንቅናቄዎች የዜጎችን አቅም በመገንባት ረገድ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ይገኛሉ ሲሉም ገልጸዋል
የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አሊ በበኩላቸው እንዳሉት ፤ በክልሉ የዲጂታልና የፈጠራ ክህሎትን ለማዳበር ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተለይም በክልሉ በስፋት እየተሰጠ ያለው የ“ኢትዮ ኮደርስ” ሥልጠና የወጣቶችን ቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅም በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገው መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል የመንግሥትን አገልግሎቶች ለማዘመን ፣ የስራ ዕድል ለመፍጠርና የሀገርን ልማት በማፋጠን በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደው በዚህ መርሃ - ግብር ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።