የቴክኖሎጂ ልማትና ተጠቃሚነትን የማጠናከር ጉዳይ የነገ መዳረሻን ለመወሰን የሚያስችል ቁልፍ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቴክኖሎጂ ልማትና ተጠቃሚነትን የማጠናከር ጉዳይ የነገ መዳረሻን ለመወሰን የሚያስችል ቁልፍ ተግባር ነው
ባህርዳር ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ የቴክኖሎጂ ልማትና ተጠቃሚነትን የማጠናከር ጉዳይ የነገ መዳረሻን ለመወሰን የሚያስችል ቁልፍ ተግባር መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ጳጉሜን 5 (የነገ ቀን) የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በተገኙበት ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የቴክኖሎጂ ልማትና ተጠቃሚነትን የማጠናከር ጉዳይ የነገ መዳረሻን ለመወሰን የሚያስችል ቁልፍ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የዛሬ ችግሮቻችን በጋራ በመፍታት የነገውን መዳረሻችንን የምንተልምበት ጊዜው አሁን ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ በተለይም ቴክኖሎጂን መፍጠር፣ በመቅዳትና በስፋት መጠቀም ይገባናል ብለዋል።
በተጨማሪም ማህበረሰባዊ ካፒታልን፣ ገንዘብን፣ የአካባቢ ጸጋን በማልማት ጥቅም ላይ የማዋል ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ባንችዓምላክ ገብረማርያም፤ የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታን ዕውን በማድረግ ነገን የተሻለ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ ትግበራዎች ውስጥ አንዱ የሆኑው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑን አንስተው ይበልጥ የማስፋትና ተደራሽነቱን የማብዛት ስራ ይሰራል ብለዋል።