ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የ2019 ዘመን መለወጫ በዓልን አብሮነትን በማጠናከር ሊያከብሩ ይገባል 

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያውያን የ2019 ዘመን መለወጫ በዓልን አብሮነትን በማጠናከርና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊያከብሩት እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

የሃይማኖት አባቶቹ የ2019 አዲስ አመት በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ እንዲሆን ተመኝተዋል። 

ኢትዮጵያውያን የ2019 የአዲስ ዘመን መለወጫ በዓልን አብሮነትን በማጠናከርና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት በአብሮነት ሊያከብሩ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የቀድሞ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳትና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ፤ ምዕመናን አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ በችግር ላይ ያሉ ወገኖቻቸውን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል። 

የ2019 አዲስ አመትን ከተቸገሩ ወገኖች ጋር በአብሮነት አዲስ ተስፋ እንዲኖራቸው ክርስቲያናዊ ተግባር በመፈጸም ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 


 

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዝዳንት ቄስ ደረጀ ጀምበሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የ2019 አዲስ ዓመትን የተጣሉትን በማስታረቅ እንዲሁም ፍቅርና አንድነትን በሕዝቡ መካከል በማስረጽ ማክበር ይገባል ብለዋል። 

በአዲሱ ዓመት ሰላምን የሚያጠናክሩ መልዕክቶችን በስፋት በማስተላለፍ  ዝማሬና ውይይቶችን ለሰላም ማጠናከሪያ ማዋል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በሀገር ውስጥ እና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለአዲሱ አመት የዘመን መለወጫ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም