ቀጥታ፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ስኬታማ ሥራ ተከናውኗል

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በ2011 ዓም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።

መርሃ ግብሩ እንደ ሀገር ያጋጠሙ በርካታ የዘላቂ ልማት ተግዳሮቶችን የመሬት መጎሳቆል የደንና ብዝሃ ህይወት መጨፍጨፍ፣ የውሃ አካላትን መድረቅና በደለል መሞላት ለመከላከል ታስቦ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል።

በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ 50 ቢሊዮን ችግኝ በማህበረሰብ ተሳትፎ ለመትከል ታቅዶ ነበር።


 

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት የመርሃ ግበሩ የትግበራ ዓመታት 56 ነጥብ 8 ቢሊዮን ችግኞችን፤ በዚህ ዓመት ብቻ ደግሞ 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኝን በመትከል በዓለም ላይ አዲስ ታሪክ ፅፋለች።

አጠቃላይ ከተተከሉ ችግኞች ከ3 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑት በአንድ ጀምበር የተተከሉ መሆናቸው በዓለም ላይ ትልቅ የችግኝ ተከላ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከተተከሉ ችግኞች 60 በመቶ የሚሆኑት የጥምር ደን ግብርና (የፍራፍሬ፣ የቡና፣ የመኖ ዝርያዎች) ሲሆኑ 35 በመቶ የደን ዝርያ ናቸው።

ይህ ታላቅ የልማት ድል የተሳካው ከላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እስከ ታችኛው የመንግስት አደረጃጀት ለመርሃ ግብሩ በተሰጠው ቁርጠኛ አመራር ነው።

በየዓመቱ ከ25 ሚሊየን በላይ ዜጎች በችግኝ ተከላ ተሳትፈዋል።


 

እስካሁን በተሠራው ሥራ በየዓመቱ ይፈጸም የነበረው የደን ጭፍጨፋ ከ92 ሺህ ወደ 27 ሺህ ሄክታር እንዲቀንስ አስችሏል።

በእርሻ ማሳ የአፈር መከላት በዓመት በሄክታር ከ130 ቶን ወደ 54 ቶን ቀንሷል።

አረንጓዴ ዐሻራ በየዓመቱ ወደ ውሃ አካላት የሚገባ የአፈር ደለል ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ቶን ወደ 208 ሚሊዮን ቶን ዝቅ እንዲል አስችሏል።

በመርሃ ግብሩ ለ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወጣቶችና ሴቶች አረንጓዴ ሥራ ተፈጥሮላቸዋል።


 

በበርካታ አካባቢዎች የፍራፍሬና የደን ክላስተር እየተፈጠረ አርሶ አደሮች የላቀ የኢኮኖሚ አቅም እንዲገነቡ እያስቻለ ነው።

ኢትዮጵያ ግዙፍ የልማት መርሃ ግብር ቀርጻ መተግበር እንደምትችል ትልቅ ተሞክሮ የተወሰደበትና ለዓለም ያሳየችበትም ነው።

ከዚህም ባለፈ ሀገራችን ዓለም እየተፈተነችበት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ተግባራዊ መፍትሔ በመስጠት ምሳሌ መሆኗን ያሳየችበት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም