ቀጥታ፡

አዲስ ዓመት-የአዲስ ተስፋ ብስራት 

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ ዓመት ዕቅዶቻችንን እና ራዕዮቻችንን በአዲስ ዕይታ እንድናድስ ተስፋ ይዞ የሚመጣ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ለማክበር ተዘጋጅተናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው እና ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች በልዩ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደተናገሩት አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ሁልጊዜ በአዲስ ተስፋ ይጠብቁታል፡፡ 

በዚህም ዕቅዶቻቸውንና ራዕዮቻቸውን የሚያድሱበት፤ አዲስ ተስፋና አዲስ ራዕይ የሚሰንቁበት በዓል በመሆኑ በተለየ ጉጉት ጠብቀው የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 


 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ፍሬሕይወት ተድላ አዲስ ዓመት ወደ አዲስ ዘመን የምንሸጋገርበትና አዲስ ተስፋ ይዞ የሚመጣ በዓል በመሆኑ በልዩ ድምቀት እንደሚያከብሩት ተናግረዋል፡፡ 


 

አዲስ ዓመት ሁልጊዜ ከአሮጌው ዓመት ትምህርት በመቅሰም ዕቅዶቻቸውንና ራዕዮቻቸውን የምንከልስበት ለአዲስ ዕቅድና ሥራ በአዲስ መንፈስ የምንዘጋጅበት በዓል ነው ያለችው ወጣት ፍቅርሰጡ ናት፡፡ 


 

አቶ ያሬድ ሙሄ በበኩላቸው አዲስ ዓመት ከዋዜማው ጀምሮ ልዩ ድባብ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ሁልጊዜ አዲስ ዓመትን ከቤተሰብና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ተሰባስበው እንደሚያከብሩት ገልጸዋል፡፡ 


 

አዲስ ዓመት ሲመጣና መስከረም ሲጠባ ሁልጊዜ ሕይወቴንና ኑሮዬን ሊለውጥ የሚችል ዕቅድ አዘጋጃለሁ ያለን ደግሞ ወጣት ሙባረክ ኸይረዲን ነው፡፡ 

የአዲስ ዓመት በዓልን ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን በአዲስ ተስፋ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብሩ የተናገሩት ወይዘሮ ገነት ገብረመድህን የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ 

 


 

አስተያየት ሰጪዎቹ፣ አዲሱ ዓመት ሲጠባ በርካታ ትዝታዎች እንደሚያስታውሷቸውም ተናግረዋል።

የዘንድሮውን አዲስ ዓመት በዓልን በልዩ ድምቀት ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ለማክበር መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም