በአፋር ክልል ዲጂታል አገልግሎትን የማስፋፋት ቅንጅታዊ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል ዲጂታል አገልግሎትን የማስፋፋት ቅንጅታዊ ተግባራት ይጠናከራሉ
ሰመራ፤ ጳጉሜን 5/2018 (ኢዜአ)፦ዲጂታል አገልግሎትን በማስፋፋት የህዝብ እርካታ ለማሳደግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ አቶ ኡመር ኑር ተናገሩ።
የጳጉሜን 5 "የነገው ቀን" በአፋር ክልል ሠመራ ከተማ "ለተቀናጀ አገልግሎት ወደ ዲጂታል መንግሥት" በሚል መሪ ቃል፣ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ድምቀት ተከብሯል።
በዕለቱ የተገኙት የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር ኑር እንዳሉት፤ "የነገ ቀን" ሲከበር በዲጂታል አሰራር የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ የህዝብ እርካታን ለማሳደግ ቁርጠኝነትን በማሳየት መሆን አለበት።
በክልሉ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎትን በመተግበር የመንግሥት አገልግሎት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
በተደመረ አቅምና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሀገራዊ ዕድገትን ለማፋጠን በአብሮነትና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑንም በአፅንኦት ገልጸዋል።
ዲጂታል አገልግሎትን በማስፋፋት የህዝብ እርካታን ለማሳደግ የተጀመሩ ቅንጅታዊ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው፣ በዚህም የነገን ቀን የተሻለ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ በዲጂታል የታገዘ የመንግስት አገልግሎት በስፋት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የበለጸገችና ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋፋት ቀልጣፋና ዘመናዊ አሠራር መዘርጋት መቻሉን ጠቁመዋል።
በዲጂታል የታገዘ ዘመናዊ አሰራር መተግበሩ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ህገ-ወጥና የተዝረከረኩ አሠራሮችን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ከፍተኛ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
በክልል ደረጃ የሚሰጡ ማናቸውም አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ መታገዛቸው ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን እያስቻለ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የ"ነገው ቀን" አከባበር መርሃ ግብር ላይ የሴክተር መሥሪያ ቤቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችና የመንግሥት ሠራተኞች ተገኝተዋል።